Search

"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ይገኛል፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ሚያዝያ 24, 2018 51

በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ አዲስ ተስፋን የሰነቀውና በሀገር በቀል የምርት ዕድገት ላይ ትኩረቱን ያደረገው "ኢትዮጵያ ታምርት" ብሔራዊ ንቅናቄ በተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያመለከቱት በአዲስ አበባ የሚገኘውን የሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞንና የኢንዱስትሪ ፓርክ የሥራ እንቅስቃሴ በጎበኙበት ወቅት ነው።
የግል ባለሀብቶች በኢንዱስትሪው ዘርፍ እያከናወኑት ያለው ተግባር የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሽግግር እያፋጠነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
30 የምርት ሼዶች ያሉት ይህ ፓርክ የግል ዘርፉ በኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ ያለውን ጉልህ ሚና የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከአግዋ (AGOA) ስምምነት መቋረጥ በኋላ ያጋጠማትን ተግዳሮት ለመቋቋም የምርት ዓይነቶችን ማብዛት ላይ ትኩረት ማድረጓን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ሁዋጂያን ፓርክ በአሁኑ ወቅት በጨርቃ ጨርቅና ጫማ ብቻ ሳይወሰን የሶላር ሴል (Solar Cell) ምርት፣ የኤሌክትሪክ ባጃጅ መገጣጠሚያ እና የተለያዩ አልባሳትን በማምረት ላይ እንደሚገኝ ተመልክተዋል።
በተለይም "ጎበዝ" (Gobez) የተሰኘው የሶላር ሴል ማምረቻ ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት 2 ጊጋ ዋት እያመረተ እንደሚገኝና በሚቀጥለው ዓመት ወደ 4 ጊጋ ዋት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
"በቪየትናም ያየነውንና የተደመምንበትን ቴክኖሎጂ አሁን በሀገራችን መተግበር ችለናል" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ፓርኩ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ፣ በኤክስፖርት የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ከውጭ ከሚመጡ ባለሙያዎች ወደ ሀገር ውስጥ የእውቀት ሽግግር በማድረግ ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተጠቁሟል።
"ኢትዮጵያ ታምርት" የሚለው ብሔራዊ ንቅናቄ በተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቀጣይ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የጀመርናቸውን ሥራዎች "ነክሶ መጨረስና" ክፍተቶችን እያዩ መሙላት ከተቻለ በሚቀጥሉት 5 እና 10 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ራሷን በራሷ የመቻል ዕድሏ ሰፊ መሆኑን ጠቁመው፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ከሁላችን የሚጠበቅ ዐብይ ተግባር መሆኑን በመግለጽ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በሃይማኖት ከበደ