Search

ከቅን ልብ የመነጨ ለወዳጅ የተከፈለ ዋጋ

ረቡዕ ሐምሌ 30, 2017 159

ለወዳጄ የመጣው እድል እንዳያመልጠው ከተረፈኝ ሳይሆን ከጎዶሎዬ ቀንሼ 54 ካሬ መሬት በነፃ ሰጥቼዋለሁ ይላሉ አቶ ከበደ ቦሮጄ፡፡
በጌዴኦ ዞን የዲላ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ናቸው አቶ ከበደ፣ ከተረፋቸው ሳይሆን ከጎደሏቸው አካፍለው በመስጠት ተምሳሌት የሚሆን ልግስናን በተግባር አሳይተዋል፡፡
የእርሳቸውን ልግስና ለየት የሚያደርገው ራሳቸውም ቢሆኑ አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ የሚመሩ መሆናቸው ነው፡፡
ከዚህም ባለፈ መሬቱ ከሚገባቸው 11 ልጆቻቸው ይልቅ አካል ጉዳተኛ እና አቅመ ደካማ የሆነ ወዳጃቸውን ለመርዳት መምረጣቸው ነው፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ሰራተኞች ከኪሳቸው ባዋጡት ገንዘብ ለ3 አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት ለመገንባት ከመረጣቸው ሰዎች መካከል በምስሉ ላይ የምትመለከቱት አካል ጉዳተኛ አንዱ ነው፡፡
ይህ ሆኖ ሲያበቃ ግን ዝናብና ነፋስ የምታስገባው ደሳሳ ጎጆው ካረፈችበት ሌላ የታሰበውን ቆርቆሮ ቤት ለመስራት የሚሆን በቂ ቦታ አልነበረውም፡፡
በዚህ ምክንያት አካል ጉዳተኛ የሆነው ወዳጃቸው እድሉ ሊያመልጠው እንደሆነ አቶ ከበደ ይረዳሉ፡፡
ይህን ጊዜ ነው ታዲያ አቶ ከበደ የልግስና እጃቸው ተዘርግቶ ከደሳሳው ቤት አጠገብ የነበረን 54 ካሬ ሜትር ቦታ ለወዳጃቸው በነጻ ሰጥተው የቤቱ ግንባታ እንዲጀመር ያደረጉት፡፡
ከተረፈኝ ሳይሆን ለራሴም አስቸጋሪ ሕይወት እየመራሁ ከጎዶሎዬ ሰጥቻለሁ ሲሉ ሀሳባቸውን ለኢቢሲ የገለጹት አቶ ከበደ፤ የተቸገረን ለመርዳት እስኪተርፈን መጠበቅ አያስፈልግም ሲሉ መክረዋል፡፡
ድጋፍ የተደረገለት አካል ጉዳተኛ በዝናብ ወቅት ቤት ውስጥ ሆኖ እንኳን የኮባ ቅጠል ደርቦ እንደሚተኛ አስረድቷል፡፡
አያይዞም አቶ ከበደ ላደረጉለት ከልብ የመነጨ ልግስና እንዲሁም የክልሉ ግብርና ቢሮ ሰራተኞች ላደረጉት ድጋፍ አመስግኗል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ቤቱን በአጭር ጊዜ ገንብቶ ከማስረከብ ባሻገር፣ የዶሮ እርባታ ሥራ እንዲጀምሩ ይደረጋልያሉት ደግሞ በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በተመስገን ተስፋዬ