በዩኒቨርሲቲዎች መካከል የሚኖረው ውድድር በትምህርት ጥራት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስገነዘቡ።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት "ከፍተኛ ትምህርት ለላቀ ተፅዕኖ" በሚል መሪ ቃል ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ጉባኤ ተጠናቋል።
በጉባኤው በትምህርት ሥርዓቱ ላይ እየተደረገ ስላለው ለውጥ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱ ተገልጿል።
በጉባኤው የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል።
በዚህም፥ ከዚህ በኋላ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያደርጉት ውድድር ባላቸው የማስተማሪያ ዕቃ እና በሕንጻቸው ብዛት ሳይሆን፤ በትምህርት ጥራት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የአስተሳሰብ መቀራረብ ሊኖር እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን፤የትምህርት ሪፎርም የመጨረሻ ግቡን በሚገባ መረዳት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ምን ዓይነት ተማሪ እያፈሩ ነው? የሚያደርጓቸው ጥናቶች ምን ያህል ወቅታዊ እና አስፈላጊ ናቸው? ጥናቶቹ ምን ያህል ዓለም ያለችበትን ሁኔታ ያገናዘቡ ናቸው? በሚለው እንዲመዘኑ ይደረጋል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲዎች የፕሮጀክት አፈፃፀም እና ከመውጫ ፈተና አሰጣጥ አንፃር የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች ድርጊቶችም መስተካከል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ባለፉት 3 ዓመታት ዩኒቨርሲቲዎች ትክክለኛና እውነተኛ መረጃ እንዲያቀርቡ ቢጠየቁም፤ ይህን እያደረጉ ባለመሆኑ በመጭው ዓመት ተጠያቂነትን እናሰፍናለን ብለዋል የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ።
በሞላ አለማየሁ