ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የቢሮው አባል በመሆን በስምምነት ተመርጣለች።
ኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆና የተመረጠችው በጄኔቫ ስዊዘርላንድ በተካሄደው የምክር ቤቱ ድርጅታዊ ስብሰባ ላይ ነው።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቡድንን በመወከል ለአንድ ዓመት ያህል በዚህ የመሪነት ሚና እንደምታገለግል ተጠቁሟል።
ኢትዮጵያ መመረጧን ተከትሎ በጄኔቫ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ቋሚ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው ዳቃ የቢሮው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እንደሚያገለግሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል።
ምርጫው ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስርዓት ውስጥ ያላትን ገንቢ ተሳትፎ እና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ በትብብር፣ በመርህ እና በባለብዙ ወገን አቀራረቦች ላይ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ሚኒስቴሩ ጠቅሷል።
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ቢሮ አንድ ፕሬዚዳንት እና አራት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን ያቀፈ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው የክልል ቡድኖችን እንደሚወክሉ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና በማገልገል ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል።