Search

ምርጫው ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት አሻራ ጥሎ ያለፈ ነው - የኦሮሚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

ረቡዕ ሰኔ 17, 2018 99

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት አሻራ ጥሎ ያለፈ መሆኑን የኦሮሚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለፀ፡፡

የኦሮሚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላሸነፈው የብልጽግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ከፍተኛ እንደነበር የጠቀሰው ምክር ቤቱ፤ የምክር ቤቱ አባላት ውጤቱን ተቀብለው ለሕዝቡ ውሳኔ ተገዥ መሆናቸውን ለክልሉና ለአገሪቱ ሕዝብ አረጋግጧል። ከዚህ በመነሳትም የጋራ ምክር ቤቱ የምስጋናና የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቶችን አስተላልፏል።

ምርጫው በሰላም ተጠናቆ ሀገራችን ስላሸነፈች ለመላው ሕዝባችን እንኳን ደስ አላችሁ ያለው ምክር ቤቱ፤ የምርጫው ሂደትና ውጤቱም ዴሞክራሲያዊና የሕዝብን ወሳኝነት ያረጋገጠ በመሆኑ የሕዝቡን ድምፅ በጸጋ እንደሚቀበል አስታውቋል። በዚህ ታሪካዊ የምርጫ ሂደት ውስጥ ለተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሁሉም ባለድርሻ አካላትም ታላቅ ምስጋና አቅርቧል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባረጋገጠው መሠረት፣ ብልፅግና ፓርቲ አብላጫውን የሕዝብ ድምፅ አግኝቶ ማሸነፉን በማረጋገጡ የኦሮሚያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለብልፅግና ፓርቲ እንኳን ደስ አላችሁ ብሏል። በቀጣይም በክልላዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ አረጋግጧል።

በአጠቃላይ 7ኛው አገራዊ ምርጫ የሕዝቡን ወሳኝነት በግልጽ ያረጋገጠና ለሁሉም አካላት ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ መሆኑን ምክር ቤቱ ጠቅሷል።

ምርጫው ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት አሻራ ጥሎ ያለፈ በመሆኑ፣ ሁሉም አካላት ይህንን ጅምር ሂደት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ መሥራትና ከምርጫ ማግስት ጀምሮ ፊታቸውን ወደ ልማትና ሰላም ግንባታ በማዞር በሁሉም ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት መትጋት ይኖርባቸዋልም ብሏል።

ብልፅግና ፓርቲም ሕዝቡ የሰጠውን አደራ በጥንቃቄ በመያዝ፣ በተለይም በሰላም፣ በሀገር ሉዓላዊነት፣ በብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም እንደ ሀገር የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር በስኬት እንዲጠናቀቅና የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሌት ተቀን ተግቶ እንዲሠራም የኦሮሚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አሳስቧል።