Search

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፉት 4 ዓመታት ከ200 ሺህ በላይ ዜጎችን በማሳተፍ የለያቸውን 8 አጀንዳዎች ይፋ አደረገ

ረቡዕ ሰኔ 17, 2018 178

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላለፉት አራት ዓመታት በመላው ሀገራችን እና ከሀገር ውጭም ጭምር በመዘዋወር የሰበሰባቸውን የምክክር አጀንዳ ግብዓቶችን መነሻ በማድረግ የተረቀቁ 8 ዋና ዋና አጀንዳዎችን ይፋ አድርጓል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ዛሬ ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ለአባገዳዎች፣ ለወጣቶች፣ ለሚዲያ ባለሙያዎች እና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሰጡት መግለጫ አጀንዳዎቹ ይፋ መሆናቸውን አብስረዋል።
ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት አካታች ሂደት መከተሉን የገለጹት ፕሮፌሰር መስፍን፣ በሂደቱም ከ200,000 (ሁለት መቶ ሺህ) በላይ ዜጎች ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አጀንዳዎቹ ከራሱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ፣ ቅሬታ፣ ፍላጎት እና ተስፋ የተቀዱ መሆናቸውንና ተአማኒነትን ለማረጋገጥ በሁሉም ክልሎች፣ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች፣ በፌዴራል ተቋማትና በዲያስፖራው ማኅበረሰብ ዘንድ ሰፊ ምክክር መደረጉን ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በተለያዩ መንገዶች ማለትም በኢሜል፣ በፖስታ፣ በስልክና በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰበሰቡ ግብዓቶች በጥንቃቄ ተለይተው የአካዳሚክና የፖሊሲ ጥናቶችን ግኝቶች ባካተተ መልኩ በኮሚሽኑ ምክር ቤት ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
እነዚህ 8 አጀንዳዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ወክለው በሚቀጥለው ሐምሌ 8 ቀን በሚጀመረው ሀገራዊ ጉባኤ ላይ ለሚሳተፉ ዜጎች እንደ መሪ ጥያቄ ሆነው የሚያገለግሉ ንዑሳን ጭብጦችን የያዙ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።