Search

የኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት ወደ ሌላ ታላቅ ምዕራፍ ተሻገረ

ሓሙስ ሰኔ 18, 2018 69

ኢትዮጵያ ወደ ዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) ለመቀላቀል እያደረገች ባለው ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ ሌላ ትልቅ እና ስትራቴጂካዊ ስኬት አስመዝግባለች።

ሀገራችን ከኒውዚላንድ ጋር በጄኔቫ በሚገኘው የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት የሁለትዮሽ የገበያ ተደራሽነት ፕሮቶኮል ተፈራርማለች።

ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን ለምታደርገው ጥረት እጅግ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑ ተመልክቷል።

ይህንን እጅግ አስፈላጊ ስምምነት በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ፀጋብ ከበበው እና የኒውዚላንድ የዓለም የንግድ ድርጅት ቋሚ መልዕክተኛ እንዲሁም የድርጅቱ አጠቃላይ ምክር ቤት ሰብሳቢ አምባሳደር ክሌር ኬሊ በጋራ ፈርመውታል።

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ፀጋብ ከበበው ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እና ግልጽ እንዲሁም በሕግ ላይ የተመሠረተ ሁለገብ የንግድ ሥርዓትን በጋራ ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ አክለውም የዓለም የንግድ ድርጅት አባል መሆን በኢትዮጵያ አሁን ላይ እየተከናወነ ባለው ሀገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ውስጥ ስትራቴጂካዊ እና ቀዳሚ ብሔራዊ ትኩረት ሆኖ እንደሚቀጥል በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የኒውዚላንድ አምባሳደር ክሌር ኬሊ ኢትዮጵያ ላስመዘገበችው ለዚህ ትልቅ ስኬት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሀገራቸው ኒውዚላንድ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን የምታደርገውን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በድጋሚ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሄዋን ጌታቸው