Search

ኢትዮጵያ ታከናውናለች፡ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች እና መዋቅራዊ ለውጦች

ሓሙስ ሰኔ 18, 2018 65

የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ባደረገው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የፋይናንስ ዘርፉን ለማዘመን እና ለማጠናከር ሰፋፊ ሥራዎችን አከናውኗል።

በዋናነት ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ከኮታ አሠራር ወጥቶ በገበያ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ተደርጓል።

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ወለድን መሰረት ወዳደረገ ሥርዓት የተሸጋገረ ሲሆን፣ ማዕከላዊ ባንኩ መንግሥትን በቀጥታ በገንዘብ ፋይናንስ ማድረግ እንዲያቆም በመደረጉ ላለፉት 24 ወራት ለገንዘብ ሚኒስቴር ምንም አይነት ብድር አልሰጠም።

በዚህም ጥብቅ የፖሊሲ እርምጃ 30 እስከ 34 በመቶ ደርሶ የነበረውን የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አሃዝ ዝቅ ማድረግ ተችሏል።

ብሔራዊ ባንክም የዋጋ መረጋጋትን ቀዳሚ ተልዕኮው አድርጎ ራሱን የቻለ ገለልተኛ ተቋም ከመሆኑም ባሻገር የፋይናንስ እና ገበያ ዘርፍ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊዎችን በመሰየም በዓለም አቀፍ የኦዲት ተቋማት በየዓመቱ ኦዲት እየተደረገ ይገኛል።

በሌላ በኩል የባንክ ኢንዱስትሪው ጤናማነት በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ ችሏል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያልተመለሰ 845 ቢሊዮን ብር የብድር ጫና የነበረበት ቢሆንም፣ መንግሥት ይህንን ብድር ወደ ቦንድ በመቀየሩ ባንኩን ከከፍተኛ ቀውስ ታድጎታል፤ ካፒታሉም በሶስት እጥፍ እንዲያድግ ተደርጓል።

የባንክ ኢንዱስትሪው አጠቃላይ ያልተመለሰ የብድር ምጣኔ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው 5 በመቶ ጣሪያ በታች በመሆን 3.07 በመቶ ላይ ብቻ ይገኛል።

የባንኮች የካፒታል ብቃት ምጣኔ ከተቀመጠው 8 በመቶ ዝቅተኛ መስፈርት በላይ በመሆን 19.1 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ የፈሳሽ ገንዘብ ምጣኔያቸውም 30.43 በመቶ መድረስ ችሏል።

በአጠቃላይ ባለፉት ስምንት ዓመታት የባንኮች የሀብት መጠን 680 በመቶ እንዲሁም የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 654 በመቶ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል።

አሁን ላይ ካለው 3.94 ትሪሊዮን ብር ብድር እና ቦንድ ውስጥ 93.8 በመቶ የሚሆነው ብድር ለግል ዘርፉ የተሰጠ መሆኑ የግል ዘርፉን የኢኮኖሚ ተሳትፎ አጠናክሮታል።

የፋይናንስ ሥርዓቱን ይበልጥ ለማስፋት ታሪካዊ የሆነው የካፒታል ገበያ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ሴኩሪቲስ ኤክስቼንጅ (ESX) ተቋቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ተገቢውን ትኩረት አጥቶ ለነበረው የኢንሹራንስ ዘርፍም ራሱን የቻለ ገለልተኛ ተቆጣጣሪ አካል ተመስርቷል።

የዲጂታል ፋይናንስ ሽግግሩን በተመለከተም አስደናቂ ለውጥ የታየ ሲሆን፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ 24.2 ትሪሊዮን ብር የዲጂታል ግብይት ተፈጽሟል፡፡

በየቀኑ በሞባይል ገንዘብ 10.6 ቢሊዮን ብር በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

እንዲሁም የመንግሥት የጡረታ ፈንድ መጠባበቂያ በሰባት እጥፍ በማደግ 470 ቢሊዮን ብር መድረስ ችሏል።

የባንክ ዘርፉን በሂደት ለውጭ ባንኮች ክፍት ለማድረግ የተወሰነው ውሳኔ ፉክክርን በመፍጠር፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና የባንክ አገልግሎትን በማዘመን የዘርፉን አጠቃላይ አቅም ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ይጠበቃል። 

በለሚ ታደሰ