ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲው ቀደም ሲል በትኩረት ማነስ ምክንያት ከዋናው የኢኮኖሚ መድረክ ተገልሎ የቆየውን የማዕድን ዘርፍ የሀገራችን ዋነኛ የልማት ምሰሶ አድርጎታል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ትገኛለች። የ2018 በጀት ዓመት ሲጠናቀቅ ደግሞ የ10.2 በመቶ ባለ ሁለት አኃዝ ዕድገት ታስመዘግባለች ተብሎ ይጠበቃል።
ለዚህ ዕድገት ዋነኛው ምክንያት ሀገራችን እየተገበረችው ያለው የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲሆን፣ ቀድሞ እምብዛም ትኩረት ያልተሰጠበትን የማዕድን ዘርፍ አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ማድረጓ ለዚህ ማረጋገጫ ነው።
ከለውጡ ቀደም ብሎ በትክክለኛ ፖሊሲ ባለመመራቱ ለብክነት እና ለሕገ ወጥ ንግድ ተዳርጎ የነበረው የማዕድን ዘርፍ አሁን እጅግ አስደናቂ የሆነ መዋቅራዊ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል።
ይህ ስኬት የተመዘገበው ዘርፉን ከነበረበት የኮንትሮባንድ እና መደበኛ ያልሆነ አሠራር በማውጣት፣ የሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት እና የብሔራዊ ሉዓላዊነት ምሰሶ እንዲሆን ለማድረግ በተወሰዱ ቆራጥ የሪፎርም እርምጃዎች ነው።
መንግሥት በሐምሌ 2016 ዓ.ም ተግባራዊ ያደረገው በገበያ የሚመራ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ እና ብሔራዊ ባንክ ለወርቅ አቅራቢዎች ያቀረበው ማበረታቻ በዘርፉ ላይ ታሪካዊ ለውጥ አስከትሏል።
ቀደም ሲል በጥቁር ገበያ እና በኮንትሮባንድ ይባክን የነበረውን ወርቅ ወደ መደበኛው የባንክ ሥርዓት ለመመለስ በተደረገው በዚህ ጥረት፣ የወርቅ ኤክስፖርት ገቢ እጅግ አስደናቂ ዕድገት በማሳየት የሀገራችን ቀዳሚ የውጭ ምንዛሬ አስገኝ በመሆን ቡናን እስከመብለጥ የደረሰ ታሪክ አስመዝግቧል።
ማዕድንን ከሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ እና ማኑፋክቸሪንግ ጋር የማስተሳሰሩ ሥራ ሌላው ታላቅ የገቢ ምርት ምትክ ስኬት የተመዘገበበት መስክ ነው።
ቀደም ሲል ለሲሚንቶ፣ ለብረት፣ ለሴራሚክስ እና ለጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ኃይል ማመንጫ የሚሆን የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ ይወጣ የነበረውን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለማስቀረት የሀገር ውስጥ ምርትን የመተካት ሥራ በሰፊው ተከናውኗል።
በዚህም የድንጋይ ከሰል የሀገር ውስጥ ገበያ ድርሻ በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 17 በመቶ በአሁኑ ወቅት ወደ 75 በመቶ አድጓል።
የአርጆ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ እንዲሁም በዳውሮ ዞን የተገነባው የኢቲ ማዕድን ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቀው በሙሉ አቅም ሥራ ጀምረዋል፡፡
እነዚህ ፋብሪካዎች የኢንዱስትሪዎችን ጥራት ያለው የኃይል ፍላጎት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተከናወኑ ስኬታማ የትስስር ማሳያዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ከባህላዊ እና አነስተኛ ደረጃ ወጥቶ ወደ ዘመናዊ እና መጠነ ሰፊ የኢንዱስትሪ ልማት እየተሸጋገረ ይገኛል።
በወለጋ የሚገኘው የቱሉ ካፒ ወርቅ ፕሮጀክት የፋይናንስ ፓኬጁን አጠናቅቆ ወደ ግንባታ የተሸጋገረ ሲሆን፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ የሚገኘው የኩርሙክ ወርቅ ፕሮጀክትም ወደ ማጠናቀቂያው እየደረሰ ይገኛል።
ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የኃይል ሽግግር ወሳኝ የሆኑ እንደ ሊቲየም (Lithium) ያሉ አረንጓዴ ማዕድናትን በማፈላለግ እና በማልማት ረገድ ሰፊ እንቅስቃሴ ጀምራለች።
እነዚህ መጠነ ሰፊ ፕሮጀክቶች ወደ ሙሉ ምርት ሲገቡ የሀገራችንን የማዕድን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጉታል።
በሌላ በኩል ዘርፉ በአሁኑ ወቅት ከ1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ ከ4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑት ደግሞ የኑሮ ዋስትና በመሆን የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ እና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በጥቅሉ ሲታይ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የተተገበሩት የማዕድን ዘርፍ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች ኢኮኖሚያዊ እሴትን ከመፍጠር ባሻገር የሀገራችንን ብሔራዊ ሉዓላዊነት እና የልማት ዋስትና ያረጋገጡ ታሪካዊ እርምጃዎች መሆናቸውን በተጨባጭ ማሳየት ችለዋል።
በለሚ ታደሰ