Search

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያለፉ ዓመታት የፋይናንስ ጉዞ፣ ከገቢ ማሳደግ እስከ ልማት ተኮር የበጀት ሽግግር

ሓሙስ ሰኔ 18, 2018 55

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 2010 እስከ 2019 በጀት ዓመት ያሳየው የፋይናንስ መረጃ፣ ከተማዋ በታሪኳ አይታው የማታውቀውን የኢኮኖሚ ዕድገትና መዋቅራዊ ሽግግር እያደረገች መሆኑን በግልጽ ያሳያል።

ይህ 10 ዓመታት ጉዞ ጠንካራ የገቢ አሰባሰብ አቅምን ከመገንባት ባለፈ፣ በጀትን አስተዳደራዊ ወጪዎችን በመቀነስ ለዘላቂ ልማት (ካፒታል) የማዋል ጤናማ የፋይናንስ ፖሊሲን የተገበረበት ነው።

መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት፣ 2010 በጀት ዓመት 40.5 ቢሊዮን ብር የነበረው የከተማዋ አጠቃላይ በጀት፣ 2019 ወደ 502.27 ቢሊዮን ብር አድጓል።

ይህ 461.77 ቢሊዮን ብር (1140 በመቶ) አስደናቂ ዕድገት ሊመዘገብ የቻለው ከተማ አስተዳደሩ የገቢ አሰባሰብ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደጉ ነው።

2010 30 ቢሊዮን ብር ብቻ የነበረው የገቢ አሰባሰብ አፈጻጸም፣ 1574.23 በመቶ (472.27 ቢሊዮን ብር) በማደግ 2019 በጀቱን በሙሉ በራስ አቅም መሸፈን ወደሚያስችልበት ደረጃ ደርሷል። ይህ የገቢ ዕድገት እና የአጠቃላይ በጀት ዕድገት መመጣጠን፣ ከተማዋ የፋይናንስ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጧን እና በውስጥ አቅም ፕሮጀክቶችን የማስፈጸም ብቃቷ መጎልበቱን ያመላክታል።

ከቁጥራዊ ዕድገት ባሻገር፣ የከተማዋን የልማት ራዕይ ይበልጥ የሚያጎላው የበጀት ድልድል ስብጥር (Capital vs. Regular Budget) ለውጥ ነው።

2010 የነበረው የካፒታል በጀት ድርሻ 53.18 በመቶ (21.53 ቢሊዮን ብር) የነበረ ሲሆን፣ ለመደበኛ ወይም ለሥራ ማስኬጃ 46.82 በመቶ (18.96 ቢሊዮን ብር) ይውል ነበር።

ነገር ግን 2019 ይህ ምጣኔ መሠረታዊ ለውጥ አሳይቶ፣ የካፒታል በጀቱ ድርሻ ወደ 71 በመቶ (355.52 ቢሊዮን ብር) ሲያድግ፣ የመደበኛ በጀቱ ድርሻ ወደ 29 በመቶ (146.74 ቢሊዮን ብር) ዝቅ ብሏል።

የአስተዳደራዊ ወጪዎችን (መደበኛ በጀት) በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ የገንዘቡን አብዛኛውን እጅ ለመሠረተ ልማት እና ለትልልቅ ፕሮጀክቶች (ካፒታል በጀት) መዋሉ፣ ከተማዋ ፊቷን ሙሉ በሙሉ ወደ እድገትና ብልፅግና ላይ ለሚታይ ትክክለኛ ልማት ማዞሯን የሚያረጋግጥ የፖሊሲ ስኬት ነው።

በአጠቃላይ፣ እነዚህ መረጃዎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሀብት አሰባሰብ አቅሙን እጅግ በላቀ ሁኔታ ከማስፋቱም በላይ፣ የተሰበሰበውን ሀብት በአግባቡ ቆጥቦ የነዋሪዎችን ኑሮ ለሚቀይሩ እና ከተማዋን ለሚያዘምኑ የካፒታል ፕሮጀክቶች ቅድሚያ በመስጠት ከፍተኛ የአመራር ብቃት እያሳየ መሆኑን በተጨባጭ የሚያስረዱ የሚያስረዱ መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።