Search

ከ123 ዓመታት በኋላ ፖላንድን የባሕር በር ባለቤት ያደረጋት የቨርሳይ የሰላም ስምምነት

ሰኞ ኅዳር 29, 2018 481

ከ16ኛው እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን ማለትም ፖላንድ ከሊቱዌኒያ ጋር ተዋህዳ በነበረችበት ጊዜ በባልቲክ ባሕር ላይ ሰፊ የባሕር ዳርቻ የነበራት፣ እንዲሁም እንደ ዳንሲግ (የአሁኑ ገዳንስክ) ባሉ ትላልቅ ወደቦች የራሷ የንግድ መርከቦች እና የባልቲክን የንግድ መስመር ለመጠበቅ የሚያስችል ግዙፍ የባሕር ኃይል ያላት ሀገር ነበረች።

ፖላንድን የባሕር በር አልባ ያደረጋት ታሪክ የሚጀምረው በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ነው።

እአአ በ1795 ዓ.ም ፖላንድ በወቅቱ ኃያላን በነበሩት ሩስያ፣ ጀርመን (የያኔዋ ፕረሽያ) እና ኦስትሪያ በተፈፀመባት ወረራ ምክንያት ግዛቷ ሙሉ በሙሉ ተከፋፍሎ፣ በባልቲክ ባሕር ላይ የነበራትን የባሕር በር አጥታ፣ ከዚያም በላይ ሕልውናዋ አደጋ ላይ የወደቀበት ጊዜ ነበር።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮም እስከ 1918 ድረስ ፖላንድ የባሕር በር አልባ ከመሆን ባሻገር ሉዓላዊነቷንም አጥታ ቆይታለች።

ለ123 ዓመታት በዘለቀው በዚህ ጊዜም ፖላንድ ዓለም አቀፍ ንግዷን የምታካሂደው ዙሪያዋን በከበቧት ሀገራት ወደቦች ነበር። ይህም ኢኮኖሚዋን ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነጻነቷንም ገድቦት ቆይቷል።

ሁኔታዎች በዚህ መልኩ ቀጥለው ፖላንድ ለ123 ዓመታት ሕልውናዋን አጥታ ከቆየች በኋላ የአንደኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቁን ተከትሎ ዳግም እንደ ሀገር የምትቆምበት ታሪካዊ አጋጣሚ ተፈጠረ።

ይህም ፖላንድን ወርረው የነበሩት ኃያላን ሀገራት በጦርነቱ መሸነፋቸውን ተከትሎ በመዳከማቸው፣ ይህን አጋጣሚ ተጠቅማ ፖላንድ በወርሃ ኅዳር 1918 ራሷን የቻለች ሀገር መሆኗን በይፋ አወጀች።

ይህን ተከትሎም ከጦርነቱ መገባደድ በኋላ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩት ውድሮው ዊልሰን አማካኝነት በተሸናፊ ሀገራት ሊተገበር የሚገባው ባለ 14 ነጥብ የቨርሳይ የሰላም ስምምነት ይፋ ሆነ።

ይህ የቨርሳይ ስምምነት ካካተታቸው 14 ነጥቦች አንዱ ፖላንድ የባሕር በር ሊኖራት እንደሚገባ የሚገልፅ ስለነበር፣ የፖላንድ የባሕር በር ጥያቄ ሕጋዊ መሠረት ሊያገኝ ቻለ።

በዚሁ መሠረት ፖላንድ የባሕር በር እንድታገኝ ያስቻለው ውሳኔ በ1919 በቨርሳይ የሰላም ስምምነት አማካኝነት እውን ሆነ።

በስምምነቱ መሠረት በጀርመን ግዛት ስር የነበረውን “የፖላንድ ኮሪዶር" የሚባለውን ጠባብ የመሬት ክፍል ለፖላንድ ተሰጠ።

ይህ ኮሪዶር ፖላንድን ወደ ባልቲክ ባሕር በቀጥታ በማገናኘት ከ123 ዓመታት በኋላ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን አስችሏታል።

በቨርሳይ ስምምነት መሠረት ለፖላንድ የተሰጠው የመሬት ክፍል የፖላንድ ኮሪደር በመባል የሚታወቅ ቢሆንም፤ ዋና ታሪካዊ ወደብ የሆነችው ግዳንስክ (ዳንሲግ) በጀርመን ተፅዕኖ ሥር "ነፃ ከተማ" ተብላ እንድትመራ ተወስኖ ነበር።

ፖላንድ በዚህ ውሳኔ መሠረት በግዳንስክ ወደብ መጠቀሟ ሊያደርስባት የሚችለውን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ጥገኝነት ለመቀነስ በ1921 ዓ.ም በኮሪደሩ የባሕር ዳርቻ ላይ ትንሽ የዓሳ ማስገሪያ መንደር የነበረችውን ገዲኒያ ወደ ዘመናዊ እና ግዙፍ ወደብነት ለመቀየር የልማት ፕሮጀክት ጀመረች።

በጥቂት ዓመታት ውስጥም ገዲኒያ የፖላንድ ዋነኛ የንግድ መስመር ሆነች።

ከዚህ በኋላም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የድንበር ማካለል ምክንያት ጀርመን የምስራቅ ድንበሯን በመቀየሯ፣ በዚህም ፖላንድ በባልቲክ ባሕር ላይ ሰፊ የባሕር ዳርቻ በማግኘቷ በአሁኑ ወቅት ፖላንድ በባልቲክ ባሕር ላይ በግምት 440 ኪሎ ሜትር የሚሆን ቀጥተኛ የባሕር ዳርቻ ባለቤት ናት።

ዛሬ ላይ በዘመናዊ መልኩ የተገነቡት እነዚህ የፖላንድ ወደቦች ሀገሪቱ በአውሮፓ በባሕር ላይ ትራንስፖርት ዘርፍ ወሳኝ ሚና እንድትጫወት አስችለዋታል።

ፖላንድ ከ123 ዓመታት በኋላ ከዜሮ እንደገና ያደራጀችው የባሕር ኃይሏም በአዳዲስ ባሕር ሰርጓጅ እና ዘመናዊ ፈንጂ ጠራጊ መርከቦች ተደራጅቶ፣ በባልቲክ ባሕር የሀገሪቱን እና የኔቶን የባሕር መዳረሻዎች እና የኢኮኖሚ ጥቅሞች የመጠበቅ ብቃት ያለው ግዙፍ ተቋም መሆን ችሏል።

በዋሲሁን ተስፋዬ

#EBC #ebcdotstream #seaaccess #seaportaccess #TreatyofVersailles #Poland #WoodroWilson