ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ሁለተኛውን የኢትዮጵያ ዲጂታል ክፍያ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል።
ምክክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ አስመልክቶ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በውጤታማነት መተግበራችን፣ ለዜጎች ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎቶችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር፣ የዕለት ከዕለት የኑሮ እንቅስቃሴን እያቀለለ ይገኛል” ብለዋል።
በተጨማሪም የኤሌክትሮኒክ እና የዲጂታል ግብይት ሥርዓትን ተመራጭ የክፍያ መንገድ እንዲሆን ማስቻሉን ገልጸዋል።
ይሄም የሕዝብን ኑሮ እና የመንግሥትን አገልግሎት ከምርጫም በላይ ብልጫ ያለው እንዲሆን እንደሚያስችለው ነው የጠቆሙት።
ባለፉት አምስት ዓመታት በተዘረጋው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ውስጥ፣ በየዓመቱ ከ18.5 ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ይሄንን ስኬት በላቀ መልኩ በማስቀጠል ሁሉን አቀፍ ብልፅግናን የማሳካት ግብ የያዘውን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁን አስታውሰዋል።
ስትራቴጂው ዲጂታል መሠረተ ልማትን የማጠናከር፣ ተደራሽነትን ብቻ ሳይሆን አጠቃቀምን ለማስፋት ክሂሎትን የመገንባት እና ችግር ፈቺ ፈጠራን የማበረታታት ዓላማ ያለው በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዲጂታል ተደራሽነት ወደ ጋራ ብልፅግና የጀመርነውን ጉዞ ለማሳካት፣ የመደመር መንግሥት በመፍጠር፣ በመፍጠን እና በእመርታ መርሕ እንደሚተጋ አረጋግጣለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።