ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለንጹህ ኢነርጂ፣ ለጤና፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪና ለምርምር ልህቀት የመጠቀም ጽኑ መሻት አላት ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ ዛሬ ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የኒውክሌር ኢነርጂ ዲፓርትመንት ኃላፊ ዶ/ር ሜካኤል ቹዳኮቭ ጋር ትብብርን በሚያጠናክሩ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ኃይልና ቴክኖሎጂን ለንጹህ ኢነርጂ፣ ለጤና፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪና ለምርምር ልህቀት የመጠቀም ጽኑ መሻት እንዳለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
ለዚህም ሀገራዊ የኒውክሌር ኃይል ፕሮግራም በቅርቡ መጀመሩንና፤ የኑክሌር ኃይል ኮሚሽንን በማቋቋምም በይፋ ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ፕሮግራሟን ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ስታንዳርድና መመሪያዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ እንደምትተገብር ጠቁመዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ሀገራችን ከኒውክሌር ኃይል ስትራቴጂካዊ ተጠቀሚነቷን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጉዞ እውን ለማድረግ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለፁላቸውም አስታውቀዋል፡፡