Search

1.2 ቢሊዮን ዶላር የተመደበለት የታንዛኒያ የዩራኒየም ማቀነባበሪያ ፕሮጀክት

ታንዛኒያ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የተመደበለት የኢነርጂ ዘርፍን እና ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ያለመ የዩራኒየም ማውጫ እና ማቀነባበሪያ ፕሮጀክት ሥራን በይፋ አስጀምራለች።
በሩሲያ መንግስት ባለቤትነት ከተያዘው የኒውክሌር ኢነርጂ ድርጅት "ሮሳቶም" ጋር በመተባበር የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ካሉ ትላልቅ የማዕድን ሥራዎች አንዱ ነው።
ተቋሙ በ20 ዓመታት ውስጥ 300 ሺህ ቶን ዩራኒየም ለማውጣት እና ለማምረት አቅዶም ሥራውን መጀመሩ ተነግሯል።
ለእቅዱ መሳካትም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን 400 ሚሊዮን ዶላር በሚገመት ወጪ የተገነባውን የዩራኒየም ማቀነባበሪያ ፋብሪካ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ይህ ፕሮጀክት ታንዛኒያ የተፈጥሮ ሀብቷን ለዘላቂነ ልማት ለመጠቀም ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ በምርቃቱ ወቅት።
የሮሳቶም ዋና ዳይሬክተር አሌክሲ ሊካቼቭ በበኩላቸው፤ ታንዛኒያ ከዓለም አቀፍ የኒውክሌር ኢነርጂ ኢንደስትሪ ጋር ለመዋሃድ ጠቃሚ እርምጃ እንድትወስድ በማገዛችን ደስተኞች ነን ማለታቸውን ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ ዘግቧል።
በታንዛኒያ የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት ኢኮኖሚያዊ እድገትን እና የኢንዱስትሪ ልማትን በማስፋፋት ሀገሪቱ ወደ ዓለም አቀፉ የኒውክሌር ኢነርጂ ገበያ እንድትቀላቀል ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በሴራን ታደሰ