በጾመ ፍልሰታ ሱባዔ ስለሀገር ሰላምና ስለሕዝብ ደኅንነት በመጸለይ፣ በልዩ ልዩ ምክንያት በመከራ ላይ ወድቀው የሚገኙ ወገኖቻችንን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ በመርዳት ሱባዔውን እናሳልፍ ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አሳሰቡ።
ፓትሪያርኩ የ2017 ፆመ ፍልሰታ መግባትን አስመልክተው ባስተላለፋት መልዕክት፥ በየጊዜው ጾምን እንድንጾም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ፈቃደ ሥጋችንን በመግራት ለእግዚአብሔር ታዛዦች እንድንሆን ነው ብለዋል።
በዚህም በሰከነ መንፈስ እግዚአብሔርን እያሰብን ኃጢኣታችንንም እያስታወስን በንስሓ ወደ እርሱ ለመቅረብና ለሱ ለመታዘዝ እንጾማለን ብለዋል።
ዛሬ በዓለም ላይ ያለው መተረማመስ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ የመጣ መሆኑን የገለፁት ፓትሪያርኩ፤ በዚህ ባለንበት ዓለም ተባብሶ የሚገኘው የመጠፋፋት ዝንባሌ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ በሰላምና በሰጥቶ መቀበል ካልተቋጨ ዳፋው አስከፊ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
አክለውም “በፍቅር ከሆነ ትንሹም ለሁሉ ይበቃልና ያለውን በጋራ በመጠቀም በፍቅርና በሰላም እንኑር፣ በጾመ ማርያም ሱባዔም ስለሀገር ሰላምና ስለሕዝብ ደኅንነት በመጸለይ፣ በልዩ ልዩ ምክንያት በመከራ ላይ ወድቀው የሚገኙ ወገኖቻችንን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ በመርዳት ሱባዔውን እንናሳልፍ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።