አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናትና ዐዳጊ ወጣቶች የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ እገዳ ጥላለች።
ይህ ውሳኔ ወጣቶችን ከዲጂታል ዓለም አሉታዊ ተጽዕኖ ለመጠበቅ የተደረገ ጥረት አካል ነው ተብሏል።
በብዙ ወላጆችና የሕጻናት መብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ የተቸረው ይህ አዲስ ሕግ፣ በአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ ኖርማን አልባኔዝ "የኩራት ቀን" ተብሎ ተወድሷል።
በአዲሱ ደንብ መሠረት ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች የከፈቷቸው የሜታ (ፌስቡክና ኢንስታግራም) እንዲሁም ቲክቶክን ጨምሮ አስር የሚደርሱ ታዋቂ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶች እንዲሰረዙ ግዴታ ተጥሏል።
ይህንን ሕግ ተላልፈው የተገኙ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች እስከ 49 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተነግሯል።
አውስትራሊያ ይህን ሕግ ለማጽደቅ የተገደደችበት ዋና ምክንያት፣ ወጣቶች ከመጠን በላይ በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ምክንያት ለተለያዩ የጤና እክሎች እየተጋለጡ በመሆኑ ነው ስትል አስታውቃለች።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ የአእምሮ ጤና ችግሮችን፣ የእንቅልፍ መዛባትና የማኅበራዊ ግንኙነት መዳከምን የመሳሰሉ ችግሮችን እያስከተለ ነው።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በአውስትራሊያ ውስጥ ከ15 ዓመት በታች ከሆኑ ዐዳጊዎችና ሕጻናት መካከል 86 በመቶ የሚሆኑት ማኅበራዊ ሚዲያን ይጠቀማሉ።
ከዚህ በኋላ ዐዳጊዎች ጊዜያቸውን በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ መጽሐፍ በማንበብ እንዲሁም የተለያዩ ችሎታቸውን በሚያዳብሩ ሥራዎች እንዲያሳልፉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ይህ ለውጥ ወጣቶች ይበልጥ ጤናማና አምራች በሆነ መንገድ እንዲያድጉ ያለመ መሆኑን የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በሃብተሚካኤል ክፍሉ