ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬት ሕገ ወጥ ንግድ እና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በጥብቅ መቆጣጠር እንደሚገባ ከኢቢሲ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር ቆይታ ያደርጉ ምሁራን ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ ባለሞያ እና መምህር የሆኑት ቆስጠንጢኖስ በርሄ (ዶ/ር)፥ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአንድ ዓመት ውስጥ የሚታዩ ለውጦች ማምጣት መጀመሩን አንስተዋል።
በፋይናንስ ፖሊሲ የተደረጉት ለውጦች በተለይም የካፒታል ገበያ ሥራ መጀመር፣ የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ መፈቀድ፣ የውጭ ኩባንያዎች በንግድ ስሥ ኢትዮጵያ ውስጥ መሰማራት ከ53 ዓመታት በኃላ የተፈቀደ እንደሆነም ነው ቆስጠንጢኖስ በርሄ (ዶ/ር) የገለጹት፡፡
እነዚህም የገበያ ዋና ምሶሶ በመሆናቸው መፈቀዱ ትልቅ ነገር ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በረጅሙ ጉዞ ትልቅ ለውጥ ያመጣልም ነው ያሉት።
ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬት ሕገ ወጥ ንግድ እና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በጥብቅ መቆጣጠር እንደሚገባም አክለዋል።
ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስቴለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ዘላቂ ሽግግር ተመራማሪ እንዲሁም ኢንቫይሮመንታል ኢኮኖሚስት የሆኑት ፕሮፌሰር ደስታ መብራቱ በበኩላቸው፤ ለኢኮኖሚ ማሻሻያው መሰረት የሆኑ ጉዳዮች ዘላቂ ለውጦች እንዲያመጡ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመፍጠር፣ የግሉን ዘርፍ ለማነቃቃት፣ የዋጋ አለመረጋጋትን ለማስተካከል እና የገቢ እና የወጪ ንግድን ለማመጣጠን፤ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ መግባት ሁነኛ መፍትሔ መሆኑንም ነው ያነሱት።
የትይዩ (ጥቁር) ገበያውን በማክሰም እና የውጭ ምንዛሬን በማሳደግ፤ የማክሮ ኢኮኖሚው ትግበራ ወሳኝ ሚና መጫወቱን የተናገሩት ደግሞ የ27 ማርኬቲንግ እና ብራንዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስቻለው ታምሩ ናቸው።
በሜሮን ንብረት