Search

በወርቃማ ጋሻ የሚጠበቀው የቻይናውያን ዲጂታል ዓለም

ሓሙስ ታኅሣሥ 02, 2018 157

ዛሬ ላይ አንድ ቻይናን የሚጎበኝ ቱሪስት ከዚህ ቀደም ሲጠቀምባቸው የነበሩት እንደ ዩቲዩብ፣ ቲክቶክ፣ ጉግል፣ ኤክስ (ትዊተር)፣ ኢንስታግራም፣ ስናፕ ቻት እና ፌስቡክ ያሉ መተግበሪያዎች ልክ እግሩ የቻይናን ምድር እንደረገጠ መሥራት ቢያቆሙበት መገረሙ አይቀርም።

ይህም የሚሆነው ከውጭ የሚመጡ የማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ለመቆጣጠርና የሀገሪቱን ዲጂታል ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በተዘረጋው የወርቃማ ጋሻ ፕሮጀክት ወይም "The Great Firewall "(GFW) በተባለው የጥበቃ ስርዓት ስለሚታገዱ ነው።

ይህ የመከላከያ ሥርዓት ከሀገሪቱ ባህል ማኅበራዊ ትስስር እና ፖለቲካዊ አመለካከቶችን ይቃረናሉ ብሎ የሚያስባቸውን ይዘቶችን  እና አስተሳሰቦችን ለመገደብ ያለመ ነው። በምትክ ደግሞ ቻይና የራሷን የዲጂታል ዕጣ ፈንታ አንድትቀርጽ ያስቻለም ዘዴ ነው።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እየታገዘ በየጊዜው ራሱን እንዲያሻሽል ተደርጎ የተሰራው ይህ የመከላከያ ሥርዓት ከውጭ የሚለቀቁ መተግበሪያዎችንና እንደ ቪፒኤን (VPN) ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ጭምር በመከታተል እና በማገድ ውጤታማነቱን አስመስክሯል።

ቻይና ከውጭ የሚመጡ የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎችን መገደብ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገር ውስጥ ፍላጎት ተስማሚ የሆኑ እና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምትክ መተግበሪያዎችን በማበልፀግም ስኬታማ ሆናለች።

በቻይና ዩቲዩብ የለም፤ በምትኩ ከቻይና ማህበራዊና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ውጭ ያልሆነ በአሊባባ ግሩፕ ስር የሚተዳደር ዩኩ የሚባል መተግበሪያ ተሰርቷል። ከ500 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወርሀዊ ተጠቃሚዎች ያሉት ይህ መተግበሪያ ዩቲዩብን ተክቶ ያገለግላል።

ከዩቲዩብ በተጨማሪም በተለይ በወጣቱ ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ቢሊቢሊ የተሰኘው መተግበሪያ ወጣቶች ከዩቲዩብ ሊያገኙ የሚችሉትን ይዘቶች ቻይና ከምትከተለው መርህ አንጻር የሚያቀርብ ተወዳጅ መተግበሪያ ሆኗል።

ሌላው በቻይና እንዳይሰሩ ከታገዱ መጠቀሚያዎች መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀው ጉግል ይገኝበታል።

በቻይና ውስጥ ጉግል በወርቃማው ጋሻ የመጠበቂያ ዘዴ እንዳይሰሩ ከተደረጉ መካከል አንዱ ሲሆን በምትኩ ባይዱ (Baidu) የሚባለው የአገር ውስጥ መተግበሪያ ተሰርቶ በወር  ከ700 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ሰወች ይጎበኛል።

በቻይና ፌስቡክ፣ ዋትሳፕ፣ ቴሌግራምና ትዊተርም አይሰሩም። በእነሱ ምትክ ዌይቦ (Weibo) እና ዊቻት (WeChat) ተተክተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል።

እንዲሁም በኢንስታግራም ምትክ ሺያኦንግሹ (Xiaohongshu) በቲክቶክ ምትክ ዶዪን (Douyin) እንዲሁም ሌሎች የውጭውን ዓለም መተግበሪያዎች ተክተው የሚሰሩ በርካታ የሀገር ውስጥ መተግበሪያዎችን በማበልፀግ በስራ ላይ እንዲውሉ አድርጋለች ቻይና።

ከዚህ ውጭ ያሉትን ከቻይና ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ እሴት ጋር አይሄዱም ያለቻቸውን  በሺህ የሚቆጠሩ  የኢንተርኔት መተግበሪያዎች በቻይና ምድር እንዳይሰሩ በወርቃማ ጋሻ የመጠበቂያ ስርዓት እገዳ እንዲጣልባቸው አድርጋለች።

ቻይና በዚህ በዲጂታሉ ዓለም የምትተገብረው ይህ  ጥብቅ የኢንተርኔት ቁጥጥር  በበርካታ ሀገራት እና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የምትተችበት ጉዳይ ቢሆንም በተቃራኒው ቻይና  ፖለቲካዊና ማህበራዊ እሴትን የሚጎዱ ይዘቶችን በመገደብ ለዜጎቿ ደህንነቱ የተጠበቀ የተረጋጋ የዲጂታል ዓለም መፍጠር ችላለች በሚል ውሳኔዋን  የሚያወድሱም በርካታ ናቸው።

በእርግጥ ሁሉን ክፍት ያደረጉ ሀገራት በማህበራዊ ሚዲያ የሚመጣባቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመከላከል በሚል ብዙ አይነት ህጎችን በማርቀቅ ተግባራዊ እያደረጉ ነው። አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ መዝጋት የሚቻልበት ዕድል ጠባብ የሆነባቸው ሀገራት በየዕለቱ ከሚመጡ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖዎች ጋር እየታገሉ ለመኖር ተገደዋል።

ከዚህ በተቃራኒው ግን እንደ ቻይና የማህበራዊ ሚዲያ ተጸኖው ሳይጎለብት ማገድ ብቻ ሳይሆን አማራጭ በማቅረብ ለነገሩ አዲስ አለመሆን እና ተቆጣጠሩልኝ እያሉ ከማመልከት ራሷ መቆጣጠር መቻሏ ብዙ ሀገራት ሊተገብሩት የሚሹት ግን ያልሆነላቸው ሆኗል።

በቅርቡ አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች ያሉ የሀገሯ አዳጊዎች እና ህጻናት ማህበራዊ ሚዲያን እንዳይጠቀሙ ህግ አውጥታ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች። ይህን ህግ ለመተግበር ግን የማህበራዊ ሚዲያ መስራች የቴክኖሎጂ ተቁማትን ማነጋገር እና ማሳመንም ይጠይቃል።

በእንግሊዝም ምሽት ላይ ህጻናት የማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ህግ ተግባራዊ ካደረገች ዓመታትን ተሻግራለች።

ይህም ሆኖ ግን ሀገራት በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት ከሚመጡ ተጽዕኖዎች ራሳቸውን ማዳን አልቻሉም።

በተለይ ደግሞ በአፍሪካ ውስጥ ይህ ተጽዕኖ ጎልቶ እናስተውላለን። የማህበራዊ ሚዲያን የሚያስተዳድሩ የቴክኖሎጂ ተቋማትም አትራፊ በመሆናቸው እና ለአፍሪካ የሚሰጡት ግምት ልክ ባለመሆኑ የችግሩ ስፋት ቀላል የሚባል አይደለም።

ታዲያ በዚህ ውስብስብ ችግር ውስጥ ማለፍ እና የሚመጣውን ተጽዕኖ ማቅለል መቻል ቀላል ሥራ ባለመሆኑ እንደ ቻይና አይነቱን ተሞክሮ ጥሩ አብነት መሆኑ አይቀርም።

ቲክቶክን ለዓለም ያስተዋወቀችው ቻይና ለዜጎቿ ግን ይህንንም እንኳ የአልጎሪዝም ለውጥ በማድረግ ነው ያቀረበቸው። በራሷ ልጆች የተበልጸገው እና ዓለም ላይ አዲስ ለውጥ ያመጣው ቲክ ቶክ በቻይና የሚሰራው ለቻይናውያን በሚሆን አልጎሪዝም እና ቋንቋ ታግዞ ተመሳሳዩ መተግበሪያ ነው።

በዋሲሁን ተስፋዬ