በአንድ የዜጎች የመለያ መታወቂያ በርካታ ተግባራትን መከወን ብሎም የአገልግሎቶች ተጠቃሚ መሆን ከተቻለ ሰነባብቷል፡፡
በተለይም እንደ ዴንማርክ፣ ኢስቶኒያ፣ ሲንጋፖር እና ሌሎች ሀገራት ዜጎች በመለያ መታወቂያቸው አማካኝነት ከ2 ሺህ በላይ ራስ አገዝ አገልግሎቶችን ለመጠቀም ችለዋል፡፡
ይህ በአንድ ጀንበር የመጣ ሳይሆን በትንሽ ጅማሬና ቀስ በቀስ እያደገ በመጣ ሂደት የዛሬውን ውጤታማ ገፅታ ሊላበስ የቻለ ነው፡፡
ዴንማርክ ምሳሌ ሊሆን የቻለውን የ"ሚት" መታወቂያን ወደ ሥራ ከማስገባቷ አስቀድሞ የነበረው የዲጂታል ጉዟዋ፣ ዜጎች እና የቢዝነስ ተቋማት ለመንግሥት አመራሮች በቀጥታ ኢሜይል መላክ የሚችሉበትን መንገድ በመፍጠር የተጀመረ ነበር፡፡
ይህ ጅማሮ ዛሬ ላይ ብዙዎች ዋቢ የሚያደርጉት የዲጂታል ሥርዓት እንድትፈጥር አስችሏታል፡፡
በዚህ የቴክኖሎጂ ውድድር ውስጥ ኢትዮጵያ ተመልካች ሳይሆን ተጠቃሚ እንድትሆን በርካታ ሥራዎችን እየሰራች ነው፡፡
በተለይም በዲጂታል 2025 ንቅናቄ ፈጣን እና ግልፅ አሰራርን ለመፍጠርም ተችሏል፡፡
በንቅናቄው የፋይዳ መታወቂያ፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት፣ የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና እና ሌሎችም አመርቂ ሥራዎች መሰራታቸውን በጅማ ዩኒቨርስቲ መምህር እና የሬቭ ፕሮ ሀብ የዲጂታል ምርምር መስራች የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ሸምሰዲን አሜ ጠቅሰዋል፡፡
የአሰራር ሥርዓቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የጊዜ እና የንብረት ብክነት እንዲቀንስ ማስቻሉን ገልፀው፤ በልፅጎ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ጉዞ የእውቀት መር ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል ስለመሆኑ ለኢቢሲ አዲስ ቀን መሰናዶ አስረድተዋል፡፡
ይህ እንዲሳካ ዜጎች እውነተኛ የሆኑ መረጃዎችን ማቀበል ላይ ተባባሪ መሆን እንዳለባቸው ነው የተናገሩት፡፡
እንዲሁም በግል ዘርፍ ያሉ ተቋማት አሰራራቸውን የዲጂታል ዘዴውን የተከተለ እንዲሆን አስፈላጊውን ጥረት ሊደርጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ24ኛው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የመሪዎች ጉባኤ፤ ኢትዮጵያ የዲጂታል ሕልሟን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችላትን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እየተገበረች መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በአፎሚያ ክበበው