Search

ለነገ ይደር የማይባለው ፋይዳን የማዳረስ ሥራ

እሑድ ታኅሣሥ 05, 2018 197

በርካታ ሀገራት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለውን ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ላይ አውለው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ዜጎች ፈጣን፣ አስተማማኝ እና ፍትሐዊ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

ደኅንነቱ የተረጋገጠ ልዩ መለያ በማቅረብ የተቀላጠፈ አገልገሎት ለማግኘት፣ ለግብይት እንዲሁም የሰነዶች ማጭበርበርን ለመከላከልም ይረዳል።

የመደመር መንግሥትም የብሔራዊ መታወቂያ ተቋም በማቋቋም ይህንን ለዜጎች ዘርፈ-ብዙ ጥቅም የሚሰጠውን ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) አገልግሎት ላይ በማዋል ላይ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መቶ ፐርሰንት እናሳካለን ብለው ካስቀመጧቸው ግቦች መካከልም አንደኛው የዲጂታል መታወቂያን መቶ ፐርሰንት ተደራሽ ማድረግ ነው።

በአሁኑ ወቅት ለ29 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ፋይዳ ተደራሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ከዚህ ቀደም በየወራት ልዩነት ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊዮን አዳዲስ ተመዝጋቢዎችን ማዳረስ ተችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመቶ ፐርሰንት ግብን ተደራሽ ለማድረግ ይፋ ካደረጉ በኋላ አሠራሩን በማሻሻል በአንድ ወር ውስጥ የሚመዘገበውን ቁጥር አራት ወይም አምስት ሚሊዮን ለማድረስ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ዳሬክተር ዮዳሄ አርአያሥላሴ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ የሚመለከተው ሁሉም አካል በተዋረድ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ዋና ዳሬክተሩ እንዳሉት ፋይዳን መቶ ፐርሰንት ተደራሽ ማድረግ ከሕፃን እስከ አዋቂ በገጠርም ሆነ በከተማ ያለ ማንኛውም ዜጋ ተደራሽ ማድረግ ማለት ነው።

በሁሉም ክልል ያለው የሕዝብ ቁጥር በዳታ የተመዘገበ በመሆኑ የፋይዳ መታወቂያን ተደራሽ ለማድረግ ክልሎች ላላቸው የሕዝብ ቁጥር ተደራሽ የማድረጉን ሥራ ተግባራዊ ያደርጋሉ።

በከተማ እና በገጠር ፋዳን ተደራሽ ለማድረግ የሚኖረው የአሠራር እስትራቴጂ የሚለያይ ሲሆን በአገልግሎት ሰጪዎች በኩልም ለማስገደድ ሕጉ ይፈቅዳል።

በመሆኑም ፋይዳን መቶ ፐርሰንት ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ለነገ የማይባል እና እንደ ሀገር የተላለፈ ግዴታ በመሆኑ በተዋረድ ሁሉም አካል ኃላፊነት ወስዶ ይሠራል።

በየክልሎች የሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎች በሕዝብ ቁጥራቸው ልክ ስትራቴጂ በመንደፍ እየተናበቡ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

በከተማዎች የሚገኙ ቀበሌዎችም በቀበሌው የሕዝብ ቁጥር ልክ ፋይዳን የማስመዝገብ ግዴታ እንዳለባቸው የብሔራዊ መታወቂያ ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርአያሥላሴ ይገልጻሉ።

ፋይዳ በማዕከል ደረጃ በ2018 በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በገቢዎች አገልግሎት (ዘርፎች) ጋር በማያያዝ እየተሠራበት ይገኛል።

በፌዴራል ደረጃም እንዲሁ ኢትዮ ቴሌኮም እና ባንኮች በኅብረት እየሠሩበት ነው።

ከዚህ ቀደም ፋይዳን ተደራሽ ለማድረግ የነበረው ዕቅድ ቀስ በቀስ ተደራሽ ማድረግ የነበረ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመቶ ፐርሰንት ግብ ካወጁ በኋላ በዚህ ዓመት ሰኔ ወር ላይ የፋይዳ ተመዝጋቢዎችን ቁጥር 90 ሚሊዮን ለማድረስ ሰፊ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Fayda #NationalID