Search

በጎረቤት ሀገራት ትብብር እና ድጋፍ የተሰራው የላኦስ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ

ሰኞ ታኅሣሥ 06, 2018 232

በማዕከላዊ ላኦስ ካሙዋን ግዛት የሚገኘውና  ላኦስን  የደቡብ ምሥራቅ እስያ ባትሪ የሚል ስያሜ ያስገኘላት የናም ቴውን 2 የኃይል ማመንጫ ግድብ የጎረቤት ሀገራት ሙሉ ድጋፍ ባይኖርበት ላይገነባ ይችል ነበር።

በደቡብ ምሥራቅ እስያ የምትገኝ ሀገር ላኦስ በግዛቷ ላይ በሚገኘው የሜኮንግ ገባር በሆነው ናም ቴውን  ወንዝ  ላይ የኤሌክትሪክ ሀይል የሚያመነጭ ግዙፍ ግድብ ለመስራት ስትነሳ ብዙ ፈተናዎች ነበሩ።

ዋናው ፈተና ላኦስ ከፍተኛ የውኃ ሀብት ያላት ሀገር  ብትሆንም ይህንን ሀብት ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል ለመቀየር የሚያስችል በቂ የገንዘብ አቅም ግን የላትም። ምክንያቱም ይህንን ግዙፍ ግድብ ለመገንባት  1.4 ቢሊየን ዶላር በላይ ያስፈልጋታል።

ስለዚህ ያላት ምርጫ ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት የፋይናንስ ድጋፍ መጠየቅ ነው። ሆኖም  አበዳሪ ተቋማት ይህንን ገንዘብ ለመስጠት ላኦስ የምታመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ ብድሩን መክፈል እንደምትችል የገበያ ዋስትና እንድታቀርብ ጠየቁ።

ከዚህ በተጨማሪም የግድቡ ግንባታ በታችኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት እንደማያስከትል ከሀገራቱ መተማመኛ ማግኘት ያስፈልጋት ነበር። በዚህ መሰረትም ጎረቤቶቿ ታይላንድ እና ቪዬትናም ጋር ውይይት ጀመረች።

ላኦስ በዚህ ውይይት በናም ቴውን ወንዝ ላይ ታላቅ ግድብ ለመገንባት እንዳሰበች የግድቡ ዲዛይንና የውኃ አያያዝ ዕቅድ እንዲሁም በአካባቢው ሥነ-ምሕዳርና ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ አንዳችም ጉዳት እንደማያስከትል የሚገልፁ ጥናቶችን በዝርዝር አቅርባ የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክቱን በመደገፍ እንዲሁም ከግድቡ የሚመነጨውን ሀይል በመግዛት ከጎኗ እንዲቆሙ ጠየቀች።

የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሆኑት ታይላንድ እና ቪዬትናም፣ የራሳቸው የኃይል ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ፣ እንዲሁም በቀረበው ጥናት መሰረት የግድቡ መገንባት በአካባቢያቸው ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ በጋራ ቁጥጥር ሊፈታ እንደሚችል በማመን በላኦስ ሀሳብ ተስማሙ።

በተጨማሪም ታይላንድ ከግድቡ የሚመነጨውን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል 93 በመቶ ያህሉን 25 ዓመታት ለመግዛት ተስማማች። በዚህም ለላኦስ አስተማማኝ ገበያ መኖሩን የሚያረጋግጥ ፊርማዋን በማኖር ወሳኝ መተማመኛ ሰጠች።

ይህ የታይላንድ የረጅም ጊዜ ስምምነት ዓለም ባንክ እና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገውን ቢሊዮን ዶላር ብድር ያለስጋት ለመስጠት እንዲደፍሩ አስችሏል። የጎረቤት ሀገር ታይላንድ ከላኦስ ጋር የገባችው የኃይል ግዥ ስምምነት የላኦስ የኢኮኖሚ ዋስትና ሆነ።

በዚህ መሰል ሂደቶች ውስጥ ያለፈው እና ላኦስ ለኢኮኖሚዋ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚሰጥ በማመን ለዘመናት ሲባክን በኖረው የውኃ ሀብቷ ላይ ልትገነባ ያሰበችው ታላቅ ግድብ በጎረቤት ሀገራት ሙሉ ድጋፍ መሰረት ከአበዳሪ ተቋማት በተገኘ የፋይናስ ድጋፍ ግንባታው 2005 የተጀመረው የናም ቴውን 2 ግድብ ግንባታ 2010 በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ።

በስምምነታቸው መሰረትም ላኦስ ከዚህ ግድብ የሚመነጨውን ከፍተኛ ሀይል ለታይላንድ በመሸጥ በዓመት በብዙ ሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ታገኛለች።

ዛሬ ላይ ላኦስ ከናም ቴውን 2 የኃይል ማመንጫ 1070 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ በማመንጨት ካሏት የኤሌክትሪክ ይል ማመንጨት ፕሮጀክቶች ሁለተኛው ግዙፍ ፕሮጀክቷ ነው። እናም ይህን ግድብ ጨምሮ በሌሎችም የሀይል ማመንጫዎች ለጎረቤት ሀገራት በሽያጭ  በምታቀርበው የኤሌክትሪክ ሀይል የደቡብ ምስራቅ ኤዥያ ባትሪ የሚል ስያሜ አግኝታለች።

ከአውሮፓውያኑ 2015 እስከ 2017 ድረስም ብዙውን ሃይል ለውጭ ገበያ በማቀረብ 170 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷንም የዓለም ባንክ ያወጣው መረጃ ያመላክታል።

የላኦስ እና የጎረቤቶቿ ትብብር በውኃ ፕሮጀክቶች ዙሪያ የፖለቲካ ውጥረት ሳያስከትል ትልቅ ልማትን ማስመዝገብ እንደሚቻል በተግባር አሳይቷል።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ