ሀገራት ሁሉ ስደተኞችን ይጠየፋሉ ብሎ መደምደም አይቻልም፤ አንዳንዶች የሚያስፈልጋቸውን የሰው ኃይል በብዙ አማራጮች ያገኛሉ፤ ከእነዚህም መካከል በስደት ወደ ሀገራቸው የሚሄዱትን ሰዎች አቅም መጠቀም ነው።
በእርግጥ ሁሉም ሀገራት የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም መሠረት አድርገው የሚሠሩ ቢሆንም ስደተኞችን የሚጠየፉ መኖራቸውም የሚካድ አይደልም። ለዚህም ነው “ሁሉም በሀገር” የሚሉ ብሂሎች በርከት ብለው የሚሰሙት።
“ምድር የተፈጠረችው ለሰው ልጆች መኖሪያነት ነው” የሚሉ ፈላስፎች፣ ሰዎች የትም ሄደው በፈለጉት ሁኔታ ውስጥ እንዲኖሩ ማቀንቀናቸው ተፈጥሯዊ ቢሆንም ይህን ሕግ ግን በሰው ሠራሽ የየሀገራት መመሪያዎች መቀየራቸው እውነት ነው።
በስደተኞች ጉዳይ ዓለም በአንድ ቋንቋ ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ቢናገርም ሀገራት ግን በጉዳዩ ዙሪያ መፍትሔም ሆነ ቢሆን የሚሉት ከሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም አንጻር ነው።
ለዚህም ነው በስደት ጉዳይ አንድ ወጥ መፍትሔ አመላካች ፍኖተ ካርታ ማግኘት የሚቸግረው።
እዚህ ላይ አውሮፓውያኑ “ከአፍሪካ የሚነሣ ስደት እኛን ያጠፋናል” ብለው እንደሚሰጉ ሁሉ አፍሪካውያን ከአውሮፓ የሚነሣ የጥፋት እሳቤ ያሳስባቸዋል። እናም የጋራ መፍትሔ ሳይሆን የጋራ ችግር ብቻ ይዞ ዓለም እንዲኖር የተከፈለበት ይመስላል።
በአፍሪካ በተለያዩ ወቅቶች ወደ አውሮፓ የሚደረጉ ጉዞዎች በሕገ ውጥ ስደት ሰንሰለት ውስጥ መያዛቸው ደግሞ “ለነፍስ ነጋዴዎች” በሰው ነፍስ መነገድ ውኃ በብርጭቆ እንደመጠጣት ቀላል ሆኖላቸዋል።
በዚህ የሕገወጥ ጉዞ ውስጥ ከግለሰብ እስከ ትላልቅ ተቋማት የሚሳተፉበት በመሆኑ ለአንዳንድ ሀገራት ችግሩን ለማስቆም አዳጋች መልክ እንዲኖረው አድርጎታል።
በዚህ መሐል ውስጥ ነፍሳቸውን አስይዘው ያላቸውን ገንዘብ ከፍለው ጉዞ የሚጀምሩ አፍሪካውያን ሕይወታቸውን እያጡ ነው የሚባል ዜና በተደጋጋሚ ቢሰማም ጆሮ ሰጥቶ ይህ ነገር ይብቃኝ የሚል ሳይሆን በዚሁ መንገድ የሚጓዝ የትውልድ አካል መኖሩ ደግሞ አሳሳቢ ነው።
በአራቱም ማዕዘናት ባሉት የመውጫ መንገዶች ሁሉ በሕገወጥ መንገድ በተለይ ወደ አውሮፓ የሚጓዙ ሁሉ የሚደርስባቸው መከራ እና እንግልት የሚነገር ባይሆንም ከሞት መትረፍ ዕድል በሆነበት መንገድ የማይታይ እና የማይሰማ ታሪክ የለም።
ከእነዚህ ታሪኮች እና የሕይወት ገጠመኞች ውስጥ የተረፉ ድምጾች የሚነግረን ተመሳሳይ ጎዳና አንድ ዓይነት ሞት እና የሕይወት ዘመን ጠባሳን ነው። እዚህ ላይ በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2023 የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ያሰቡ ድምጾች ሁሌም ይነሣል።
በዚህ ወቅት 101 ሴናጋላውያንን የያዘችው አነስተኛ ጀልባ አቅጣጫዋን ወደ ካናሪ ደሴቶች በማድረግ ጉዞዋን ጀመረች።
ከእንጨት በተሠራችው አነስተኛ ጀልባው ውስጥ በአብዛኛው ወጣት ወንዶችና ታዳጊዎች ነበሩበት። የሁሉም ህልም የስፔን ግዛት ወደሆነው ካናሪ ደሴት መድረስ ነው። ጉዟቸው አንድ ሳምንት ብቻ እንደሚወስድ በተነገራቸው መሠረትም ለዚህ ጉዞ የሚሆናቸውን ሩዝ እና ለመጠጥ የሚሆን ውሃ ይዘዋል።
ሴኔጋላውያኑ መንገደኞች በዚህ አደገኛ የሆነ የባሕር ጉዞ ሊያጋጥማቸው ከሚችለው አደጋ ይልቅ በስፔን ወይም በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ሊኖራቸው ስለሚችለው የተሻለ ሕይወት ብቻ እያሰቡ ጉዟቸውን ቀጠሉ።
ሆኖም ከጥቂት ቀናት የባሕር ጉዞ በኋላ ለዚህ አይነት አስቸጋሪ ጉዞ ያልተሠራችውና ከመጠን በላይ ጭነት የተሸከመችው ጀልባ ሞተሯ መበላሸት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ለባሕር ጉዞ ዋና አስፈላጊ መሳሪያ የሆነው አቅጣጫ ጠቋሚ የጂፒኤስ መሳሪያ ስራ አቆመ።
በአትላንቲክ ውቅያኖስ ያለአቅጣጫ አመላካች ኮምፓስ መጓዝ ፈፅሞ የማይታሰብ ነገር በመሆኑ ጉዟቸው ወደማይሆን አቅጣጫ ማምራት ያዘ። ሞተሯ ብልሽት የገጠመው ጀልባ ንፋሱ ወደሚወስዳት መሄድ ጀመረች።
ሰባት ቀን ብቻ እንደሚፈጅ የታሰበው ጉዞ የማይሆን ሆነ። ቀኑ ይመሻል ሌሊቱ ይነጋል ፀሐይና ብርድ እየተፈራረቀባቸው ወደየት እንደሚጓዙ ቀርቶ የት እንዳሉም ማወቅ ተሳናቸው። በዚህ ሁኔታ እያሉም ለሳምንት የያዙት ምግብና ውሃ አለቀ።
በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ያላንዳች ምግብና ውሃ፣ ወጀብና ነፋስ በሚወስዳቸው አቅጣጫ እየሄዱ ከቆዩ በኋላ አንዳንዶቹ አዕምሯቸውን መሳት ጀመሩ። ጥቂት የማይባሉት በተስፋ መቁረጥ ራሳቸውን ወደ ውቅያኖሱ ወረወሩ። ህመም፣ ረሀብ፣ ስቃዩና መከራው ከሚችሉት በላይ የሆነባቸው በእንጨት ጀልባቸው ላይ ሆነው ለዘለዓለሙ አንቀላፉ።
በሕይወት የተረፉት ቀሪዎቹ በስቃይና በተስፋ መቁረጥ በሞት የተለዩትን የጉዞ ጓደኞቻቸውን አስከሬን ወደ ውቅያኖሱ በመጨመር ተሰናበቷቸው። በወዳጆቻቸው ሀዘን ለማልቀስ የሚያስችል አቅም እንኳን አልነበራቸውና በዝምታ አነቡ።ነገ የእነሱም ዕጣ-ፈንታ ምን እንደሆነ የማያውቁት የተሻለ ሕይወት ፈላጊ ወጣቶች የሳምንቱ ጉዞ ሁለት ሳምንት ወር እያለ ለ36 ቀናት በባሕር ላይ ጠፍተው ከረሙ።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ለ36 ቀናት ጠፍታ የነበረችውን ጀልባ ሲያገኙ ሴኔጋል አንድ መቶ አንድ ሆነው ተነስተው ቀስ እያሉ እያለቁ የቀሩት 38 ሰዎች ብቻ ነበሩ። እነሱም በውቅያኖስ ጨዋማ ውሃ ፊታቸው ተቃጥሎ በፀሐይና ብርድ ተጎሳቁለው የደከሙና በከፍተኛ ሁኔታ የታመሙ ነበሩ። ይህም ሆኖ ዋናው ጥሩ ነገር እና ዕድለኛ ሆነው ነፍሳው ብቻ አለች።
በዚህ ሁኔታ በሕይወት ከተረፉት ውስጥ አንዱ ሲናገር፦ “ቤተሰቦቻችንን ተሰናብተን ከሴኔጋል ስንነሣ የሚታየን ጉዟችን ተሳክቶ በአውሮፓ ሀገራት ስለሚያጋጥመን ብሩህ ሕይወት ብቻ ነበር። እንዲህ አይነት አስፈሪ ቅዠት የሚመስል ነገር እንደሚያጋጥመን ብናውቅ ከሀገራችንም ባልተነሣን ነበር። በዚህ አደጋ ከሞቱት ውስጥ አንዱ የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ አብሮኝ የተሰደደው ጓደኛዬ ይገኝበታል። የመጨረሻ እስትንፋሱን ሲወጣም እያየሁት ነበር። ብዙ ህልም ያላቸው ሰዎች በሞት አጥተናል። ምናልባት እኔም በሕይወት የተረፍኩት ይህንን አሳዛኝ ክስተት ለሌሎች እንድመሰክር ይሆናል።” በማለት በሕገ-ወጥ መልኩ ስደትን ለሚያስቡ ሰዎች የጉዞውን አስከፊነት ተናግሯል።
በዚህ አይነት ሕይወትን ለአደጋ የሚያጋልጥ ጉዞ ውስጥ አልፈው የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ የሚሰደዱ አፍሪካውያን ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ በመሄዱ የአደጋው ተጋላጭ ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል።
እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅ (IOM) መረጃ ከ2014 ጀምሮ ከሀምሳ ሺህ በላይ አፍሪካውያን በሕገወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት በሚሞክሩበት ወቅት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የዚህ የሕገወጥ ስደት ሰለባ ሆነው በተለያየ ጊዜ ክቡር ሕይወታቸውን በባሕርና በመንገድ ላይ ታጣቂዎች እያጡ ከሚገኙ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች መሀከል ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል።
ከቀናት በፊትም በዚሁ አይነት ሁኔታ ወደ ሳዑዲ ለመጓዝ አስበው ጉዞ የጀመሩ 154 ኢትዮጵያውያንን የጫነች ጀልባ በየመን የባሕር ዳርቻ በመስጠሟ በሕይወት ማግኘት የተቻለው 12 ሰዎችን ብቻ ነበር።
ከዓመታት ጀምሮ እስካሁንም በቀጠለው በዚህ ያልተዘጋው የሞት መንገድ ሊያጋጥማቸው ከሚችለው የተሻለ ሕይወት ይልቅ አደጋው እንደሚያመዝን ቢታወቅም ከእለት ወደ እለት ቁጥሩ እየጨመረ ይገኛል።
መንግሥት ይህንን ሁኔታ ለመቀነስ እያደረገ ባለው ጥረት ከውጭ ሀገራት ጋር ህጋዊ የሥራ ስምምነት ውል በመፈራረም ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈላጊዎች በህጋዊ መልኩ መስራት እንዲችሉ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ይገኛል።
በዚህም መሠረት ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬት፣ ከዮርዳኖስ፣ ከሊባኖስ፣ ከኳታር እና ከኩዌት መንግሥታት ጋር የሁለትዮሽ የሥራ ስምሪት ስምምነት በመፈራረም ወደ ሥራ እንዲገባ የተደረገ ተደርጓል።
በ2014 ዓመት 69 ሺህ 718፣ በ2015 ዓመት 102 ሺህ 076፣ በ2016 ዓመት 345 ሺህ 167 እንዲሁም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 503 ሺህ 173 ዜጎች መንግሥት በዘረጋው ህጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ስርዓት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር መረጃዎች ያመላክታሉ።
በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት መጓዝ ክቡር ሕይወትን ከመታደግ ባለፈ ትናንሽ ችግሮች እንኳን ቢከሰቱ ለመፍታት ብዙ ሰርቀትን መጓዝ አይጠይቅም። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ከሰሞኑ በሳዑዲ አረቢያ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ተፈጽሞባት ካሳ ያገኘችው መካ መሃመድ አራጋው ነች።
መካ ወደ ሳዑዲ በህጋዊ መንገድ ከሄደች በኋላ ያጋጠማትን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያየው በሳዑዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲው ጉዳዩን በቀላሉ አልተመለከተውም።
እዚህ ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ጉዞዋን በሕጋዊ መንገድ ያደረገችው መካ መሃመድ መሉ መረጃዋ እሷ ሳዑዲ ከመድረሷ በፊት ለኤምባሲው ደርሶት ስለነበር ጉዳዮን ወደ ፍትህ በመውሰድ ነበር የጀመረው።
ያቀረበውን ክስ መሠረት አድርጎ የሳዑዲ አረቢያ የጸጥታ አካላት ክትትል በማድረግ በመካ መሃመድ ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩትን ሁለት ሴቶች በቁጥጥር ሥር በማዋል ተበዳይ መካ መሀመድን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ኢምባሲ ቅጥር ጊቢ እንድትመለስ ማድረግ ችሏል።
በሂደቱም የመካ መሀመድ አሰሪዎች የፈጸሙትን ኢ-ሰብዓዊ ተግባር በማመናቸው እና በመፅፅታቸው በቤተሰብ ደረጃ በድርድር እንዲያልቅ ለኢምባሲው ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል።
መካ መሀመድ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ ተጠይቃ በመፍቀዷ 20 ሺህ የሳዑዲ ሪያል የሞራል ካሳ እንዲከፈላት በማድረግ እርቅ ማውረድ እና ፍላጎቷ የነበረው ወደሀገር ቤት የመመለስ ጥያቄዋን ኤምባሲው አመቻችቶላታል።
እዚህ ላይ ትልቁ ቁም ነገር እሷ እንኳን ወደ ኤምባሲ መሄድ ባታስብ እና ባትችል ኤምባሲው ችግሯን አይቶ እንዳያልፍ ብሎም ያለችበትን በሂደትም ለማወቅ እንዲችል ቀድሞውኑ መረጃዋ ስላለው ጉዳዮን በቀላሉ ፍትህ ለማሰጠትም እንዲችል አድርጎታል።
በህጋዊ መንገድ መሄድ ጠቀሜታው ይህ ነው ይህ ነው ተብሎ የሚተነተን አይደለም። ምክንያቱም እንደ መካ መሀመድ ሁሉ ከብዙ ችግር ውስጥ ከመውጣት እስከ ሕይወትን መታደግ የደረሰ ብዙ ነው። ለዚህም ነው መግሥት ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው መለወጠን ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ በህጋዊ መንገድ ብቻ የሚደረግ ጉዞን ነው የሚደግፈው።
መደገፍ ብቻም አይደለም ህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪቶችን ለማድረግ የሚያስችሉ ስምምነቶችን ከተለያዩ ሀገራት ጋር በማድረግ ይፋ አድርጓል።
ይህም በመሆኑ መንግሥት በቀጣይ የስራ ስምሪት መዳረሻዎችን ለማስፋት የሚያደርገው ጥረት እንዳለ ሆኖ እስከዛው ግን ዜጎች መንግሥት ካወጣው ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ውጭ በሌሎች በተሳሳቱ መረጃዎች ተታለው ባለመሄድ ክቡር ሕይወታቸውን ከአደጋ መጠበቅ ይገባቸዋል።
#EBC #ebcdotstream #refugees #immigration #death