የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚንስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው ኢትዮጵያን ወክለው በሦስተኛው በማደግ ላይ ያሉ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ይገኛል።
በጉባዔው የባሕር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ እና በቂ የመሠረተ ልማት አለመሟላትን ጨምሮ ከባድ ፈተናዎች እያጋጠሟቸው መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በባሕር ላይ ያለው ሃብት ለሁሉም ሀገራት በቂ ከመሆኑም ባሻገር ብልጽግናን እንደሚያመጣ ኢትዮጵያ እምነት አላት ያሉት ሚኒስትሩ፥ ዋስትና ያለው እና ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር በር የማግኘት መብት መከበር እንዳለበትም ጠቁመዋል።
አክለውም የባሕር በር ማግኘት ሁለንተናዊ የሉዓላዊነት ማረጋገጫ መብትም ነው ብለዋል።
የባህር በር ተጠቃሚነት ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለባህር አዋሳኝ አካባቢዎች ደህንነት መጠበቅ ወሳኝ መሆኑንም ሚኒስትሩ።
ኢትዮጵያ ከዚህ ጉባዔ የለውጥ ውሳኔዎች እና አዲስ ዓለም አቀፋዊ ቁርጠኝነት እንደምትጠብቅም አንስተው፤ ሀብቶቻችንን የሚያሳድጉ አዳዲስ ውጤታማ ወዳጅነቶችን እንደምናፈራም ተስፋ አለን ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ጉባዔው ባፀደቀው “የአዋዛ የድርጊት መርሐ ግብር” መሠረት፤ ሁሉም ሀገራት በእኩልነት የባሕር በር የመጠቀም መብትታቸውን ለማረጋገጥ የቀረበውን ሀሳብ ታወድሳለችም ብለዋል ሚኒስትሩ።
ፍትሐዊ የባሕር በር ተጠቃሚነት ቀጠናዊ ውህደትን ለማጠናከር እና ንግድን ለማሳለጥ የሚያስችል በመሆኑ፤ ይህን መብት የሚያረጋግጥ የሀሳብ ለውጥ እንጠብቃለንም ሲሉም ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በሰለሞን ከበደ