አንድን ማህበረሰብ ለጋራ ዓላማ ለማሠለፍ የሥነ ልቦና ውቅር መቅረጫ ስልት ነው ነው ይሉታል ትርክትን ሲበይኑት ባለሞያዎች፡፡ እናም ትርክት ታሪክ ማለት ሳይሆን የታሪክ አረዳድ ወይም ግብ ያለው የታሪክ አረዳድ እንደሆነ ብዙዎችን ያግባባል።
ለዚህም ነው ሀገራት ሲሰሩ አንድ ትርክት በመፍጠር ማህበረሳባቸውን ለአንድ ዓላማ ለማሰለፍ ሲተጉ የምናስተውለው። በእርግጥ እዚህ ላይ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዕለ ሃያል ከሆነችው አሜሪካ ጀምሮ የእስያ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ጭምር ትርክትን ተጠቅመው ዓለም ላይ ገናና መሆን ችለዋል።
ዛሬ በዓለም ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ መድረኮች ላይ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነችው ቻይና በጎሳ በቋንቋና በባህል ልዩነት ከመከፋፈል ይልቅ በአንድነት መቆም የቻለችው በጠንካራ ሀገረ መንግሥት ምስረታ ላይ ያተኮረ ብሔራዊ ትርክትን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ ማኒፌስቶ አማካኝነት ነው።
ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ እስከ 1949 ድረስ የነበረው ጊዜ ቻይና በእርስ በርስ ግጭት ተዳክማ አንድ ባለመሆኗ ምክንያት በውጭ ኃይሎች በተደጋጋሚ ተሸንፋ የሀገሪቱ ሉዓላዊነት ተገፍፎ የቆየበት ዘመን ነበር።
ቻይናውያን 'የውርደት ዘመን' Century of Humiliation በሚል ስያሜ በሚያስታውሱት በዛን ወቅት ኢኮኖሚው በጦርነትና በፖለቲካዊ አለመረጋጋት በመውደቁ ሀገሪቱ በዓለም ላይ ካሉ ደሃ አገራት መካከል አንዷ ነበረች።
በተጨማሪም የጎሳና የክልል ጦር አበጋዞች በሚፈጥሩት ልዩነት አንድነቷ ተናግቶ ስለነበር በቀጣይ እጣ ፈንታዋ ላይ መላክም ለማሰብ በሚከብድበት ሁኔታ ውስጥ ስለመውደቋም ይነሳል።
ሆኖም በ1949 የማኦ ዜዱንጉን ወደስልጣን መምጣት ተከትሎ በቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ (CCP) አማካኝነት የተገነባው ብሔራዊ ገዥ ትርክት ቻይናን ከዚህ የውድቀት አረንቋ ለማውጣት ችሏል።
ይህ ገዥ ትርክት የብዙ ሺህ ዓመታት የሥልጣኔ ባለቤት የሆነችውን ቻይናን የጋራ ብሔራዊ ክብርን በማጉላት የተባበረ አንድነትን መፍጠር ቻለ።
ለሁሉም ቻይናውያን ከጎሳና ከክልል ልዩነት ባሻገር ብሔራዊ ማንነትን በመስጠት፣ "እኛ ማን ነን?" ለሚለው ጥያቄ የማያሻማ እና የጋራ መልስ ሰጠ። የጎሳ እና የክልል ፍላጎቶች ሁሉ በብሔራዊ አንድነት ሥር እንዲገዙ በማድረግ የተከፋፈለችውን ሀገር ሰበሰበ።
በዚህ መሰረት በማኦ ዜዱንግ እሳቤ የብሔራዊ አንድነት መሠረቷን በሚያጠናክር ገዥ ትርክት ከመከፋፈል የወጣችው ቻይና በ1978 ወደ ስልጣን በመጣው በዴንግ ዚያኦፒንግ የተቀረፁትን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ለመተግበር አላስቸገራትም።
ቻይና በዚህ በትውልድ ቅብብሎሽ የአንድነቷ መሰረት ተጠናክሮ ከ800 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን ከከፍተኛ ድህነት አውጥታ ከበለፀጉ ሀገራት ተርታ መሰለፍ የምትችል ሀገር ሆናለች።
እናም ቻይና የውርደት ዘመኗን ረስታ ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ መድረክ ልዕለ ኃያል ሀገር መሆን የቻለችው መከፋፈልን አስቀርቶ አንድነትን አላማ ባደረገ ገዥ ትርክት አማካኝነት ነው።
ቻይናውያን በዓለም መድረኮች ሁሉ የሚፈለጉ እና አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚሄዱ ያለፉበትን መጥፎ ታሪክ ሌላ ሀገር ላይ የተፈጠረ እስኪመስል ድረስ አልፈውት ሃያልነታቸው ላት አተኩረዋል።
ለዚህ ሃያልነታቸው ደግሞ ያኔ እያመማቸውም ቢሆን የወሰኑት ውሳኔ እና የተራመዱበትን መንገድ በገዥ ትርክት አጽንተው መጓዛቸው ቀዳሚው ምስጢር ነው።
በዋሲሁን ተስፋዬ