በኢትዮጵያ የተጀረው የውጭ ምንዛሬ ሪፎርም በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ ገለፁ።
የባንኩ ገዢ በሰጡት ማብራሪያ፤ በ2017 በጀት ዓመት የባንኩ የውጪ ምንዛሬ የመጠባበቂያ ክምችት በሶስት እጥፍ ማደጉን አስታውቀው፤ ይህ አበረታች ሁኔታ በአዲሱ በጀት ዓመት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ባንክ የውጪ ምንዛሬ ፍሰት እና ግኝት ከተጠበቀው በላይ ማደጉን ተናግረው በአዲሱ በጀት ዓመት የውጭ ምንዛሬ ጨረታ እንዳስፈላጊነቱ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።
አክለውም ከውጪ ምንዛሬ ገቢያችን ከፊሉን ለባንኮች በጨረታ ማቅረባችን በባንኮች ዘንድ የሚኖረውን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ከማሳደግ ባሻገር ዋጋን እና የውጭ ምንዛሬ መረጋጋትን አስፍኗል ብለዋል።
በቅርቡ በተደረገ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ 28 ባንኮች መሳተፋቸውንም አንስተዋል።
በጨረታው 150 ሚሊዮን ዶላር እንደተሸጠ እና ባንኮች የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሬ ያገኙበት መሆኑን አስታውቀዋል።
የውጭ ምንዛሬ ጨረታውን ያሸነፉ ባንኮች በጨረታ ያገኙትን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ጨምረው በቀጣይ ሳምንት ለደንበኞቻቸው እንደሚያቀርቡ አቶ ማሞ ምህረቱ ገልፀዋል።
በሔለን ተስፋዬ
#EBC #ebcdotstream #NationalBankofEthiopia