Search

የበቀል መንገድን የዘጋው ሀገራዊ ምክክር

ዓርብ ታኅሣሥ 10, 2018 30

በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ለነፃነታቸው በብርቱ ቢታገሉም ከነፃነት ማግስት ግን እንዳሰቡት የሰላም አየርን ለመተንፈስ አልታደሉም።

አንድነትን ያጠፋው የቅኝ ግዛት ካሳረፋቸው ጠባሳዎች አንዱ የዜጎች በዘር፣ በሃይማኖት እና ጎሳ መከፋፈል ነበር።

ይህ ከትናንት እስከ ዛሬ በአህጉረ አፍሪካ ያሉ ሀገራት ለሚናጡባቸው ግጭቶች መነሾ ነው።

ወንድማማች እና እህትማማች ሕዝቦች ደም ሲቃቡ ብዙ ሀገራት ከመበተን ጫፍ ደርሰው ነበር።

ይህንን ስጋት ለመግታት የተደረጉ ሀገራዊ ምክክሮች ሀገራቱን ከመበተን አድነው የበቀል መንገድ እንዲዘጋ ማድረግ ችለዋል።

ደቡብ አፍሪካ ለዚህ በዋቢነት የምትጠቀስ ቀዳሚ ሀገር ናት። ከአፓርታይድ በኋላ በጥቂት ነጮች ሥር የዋለው የመሪነት ሚና አብዛኛው ደቡብ አፍሪካውያን በፖለቲካዊ ተሳትፎ፣ በማኅበራዊ መስተጋብር እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ይገለሉ ነበር።

በዚህ ምክንያት የተንሰራፋው መገዳደል፣ ሕገ-ወጥ እስር፣ ሽብርተኝነት እና ሌሎችም አሉታዊ ድርጊቶች የሀገሪቷን የመቆም ሰበዝ ያላሉ ነበሩ።

“በእንደዚህ ዓይነት ወቅት መነጋገር ድክመት ሳይሆን የችግር መውጫው ነው” በማለት .. 1991 እስከ 1992 የዴሞክራቲክ ደቡብ አፍሪካ ኮንቬንሽን (Convention for a Democratic South Africa) ተካሄደ።

ይህም ሀገሪቷን ከመበተን ታድጎ የበቀል መንገድ እንዲዘጋ አስችሏል።

የሩዋንዳ፣ ኮሎምቢያ እና የኬንያ ሀገራዊ ምክክር ምን ማድረግ እንደቻለ ሌላው ማሳያ ነው።

ወደ ሀገራችን ስንመጣ ኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያስተናገደቻቸው ግጭቶች እና የታሪክ ቁርሾዎች እንዲታከሙ በማሰብ እየመከረች ትገኛለች።

ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል በአጀንዳ ልየታው ያካታተው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በየአካባቢው በመዝለቅ የግጭት እና ያለመስማማት መንስዔዎችን አንጥሮ ለይቷል።

በዚህም በተቻለ መጠን በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸውን የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ይገልጻሉ።

በቀጣይ የትግራይ ክልል አጀንዳ ልየታ የሚካሄድ ሲሆን እርሱን ተከትሎ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ እንደሚካሄድ ዋና ኮሚሽነሩ በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።

የአጀንዳ ልየታ ከመጀመሩ በፊት በምክክር መንገድ አልፈው ውጤታማ ሊሆኑ የቻሉ ሀገራት ተሞክሮ ታይቷል።

ይህን መሰል ውይይት በሀገራችን የመጀመሪያው በመሆኑ በርካታ ተግዳሮቶች ስለመስተናገዳቸውም ፕሮፌሰር መስፍን አስታውሰዋል።

እግር በእግር የሚከተል ግጭት ዋነኛ ፈተና እንደነበር ገልጸውም፣ በኮሚሽኑ ውስጥ የመንግሥት እና የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር መደረጉ ችግሮቹ በቀላሉ እንዲታለፉ ስለማድረጉ ነው የተናገሩት።

ግዳጁ ሊያበቃ የጥቂት ወራት ዕድሜዎች የቀሩት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከሀገራዊ ጉባዔው በኋላ የሚገኙ አጀንዳዎችን ለሕግ አውጪው የመንግሥት ክፍል የማስረከብ ሥራን የሚሠራ ይሆናል።

ከትግራይ ክልል ውጪ ካሉ የሀገሪቷ አካባቢዎች የተውጣጡ ወደ 4 ሺህ 500 የሚሆኑ የሕዝብ ተወካዮች የዜጎችን አጀንዳ ይዘው በሀገራዊ ጉባዔው ላይ ይሳተፋሉ።

እርሱን ተከትሎ ኮሚሽኑ የሚኖሩበት ኃላፊነቶች በሕዝብ ተወካዮች አማካኝነት የሚቀመጥ ሲሆን ከዚያ በተረፈ ለሕግ አውጪው አካል የተላለፉ ጉዳዮች የደረሱበትን የአፈፃፀም መጠን የሚከታተል ይሆናል። 

በአፎሚያ ክበበው 

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #dialogue #elders #peace