ቀድሞ የባህር በር ባለቤት የነበረችው ኅብረብሔራዊት ኢትዮጵያ፣ በተሳሳተ ትርክት ምክንያት ላለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት ከባህር ተገፍታ ቆይታለች። ይህም ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ማስከተሉን ምሁራን ይገልጻሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባህር በር ጉዳይን አስመልክቶ ቀደም ሲል በሰጡት ማብራሪያ፤ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በጂኦግራፊያዊ እስር ቤት ውስጥ ሆና መቀጠል እንደማትችል መግለጻቸው ይታወሳል።
የባህር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና የጋራ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሰጥቶ መቀበልን መሠረት ያደረገ የባህር በር ባለቤትነት አስፈላጊ መሆኑን በጽኑ አስምረውበታል።
የመደመር መንግሥት በጀመረው የብልፅግና ጉዞ፣ ለባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።
የዓለም የሰላም አምባሳደር እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ስለሺ ዑመር ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና የሕዝብ ብዛት መጨመር የባህር በር ባለቤትነትን አስገዳጅ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ይህ ጉዳይ የግለሰብም ሆነ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ወደብ አጥታ በመቆየቷ ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጓን አቶ ስለሺ አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ኅብረብሔራዊት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ እያመዘገበችው ያለውን ለውጥ ዘላቂ ለማድረግ፣ የባህር በር ጥያቄ የህልውናዋ መሠረት በመሆኑ ተገቢው ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል።
የትውልድ ጥያቄ በሆነው የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ላይ እሳቤያችንን በማስተካከል ለመብታችን በሰላማዊ መንገድ መታገል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህም ባለፈ የባህር በር መኖር ለሉዓላዊነት መጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለው አያይዘው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ በመመሥረት፣ ከጎረቤቶቿ ጋር አብሮ የማልማትና በጋራ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት አቶ ስለሺ አንስተዋል።
የታሪካዊ የባህር በር መብት ጥያቄው ፍትሐዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ የጥንቱ የኢትዮጵያ ዕድገትና ሥልጣኔ የባህር በር ለሀገር ዕድገት ያለውን አስፈላጊነት ሕያው ምስክር ነው ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ለጀመረችው የብልፅግና ጉዞና ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋ የባህር በር ባለቤትነት የግድ አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
በሜሮን ንብረት