Search

ሀገር በቀል የሕክምና ዕውቀትን በዘመናዊ መንገድ መምራት፤ የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የፋርማሲዩቲካል ምርምሮችና የሚዲያው ሚና

ሓሙስ ሰኔ 11, 2018 42

የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት "ምርምር እና ሚዲያ ለላቀ ጤና" በሚል መሪ ቃል አራተኛውን ዓመታዊ የሚዲያ ፎረም እና የጉብኝት መርሐ-ግብር በአለርት ሆስፒታል አካሄደ።

መርሐ-ግብሩ ተቋሙ የሚያከናውናቸው ውስብስብ የሳይንስ፣ የሕክምናና የፋርማሲዩቲካል ምርምሮች “በቀላል ቋንቋ” ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑና የሚዲያ ባለሙያዎች ስለ ሥራው ጥልቅ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ለማስቻል የተዘጋጀ ነው።

May be an image of one or more people, people studying, hospital, newsroom and text that says 'AAJAT 10 Labe Labotronics tranics Electrolyte ElectrolyteAnalyzer Analyzer ELA-001 AR-TGELA'

ኢንስቲትዩቱ  ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እና ምክትል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዓለምሰገድ አብዲሳ እንደገለጹት፤ ሕክምና ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው የቀደሙ ሥልጣኔዎች አንዱ ቢሆንም ዘመናዊ መንገድ ባለመከተሉ ወደፊት መጓዝ ሳይችል ቆይቷል፤ አሁን ግን መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረት ሀገር በቀል ዕውቀትን በዘመናዊ አግባብ መምራት ተችሏል።

ኢንስቲትዩቱ የመድኃኒት፣ የክትባትና የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪውን በስፋት እየደገፈ ይገኛል።

ባለፈው መጋቢት ወር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀው ዘመናዊው ባለ 8 ወለል የላብራቶሪ ሕንጻ ለሀገርና ለመላው አፍሪካ ትልቅ አቅም የፈጠረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የሬቢስ ክትባትና የዕባብ መርዝ ማከሚያ በአገር ውስጥ ለማምረት ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በክትባት ራሷን እንድትችል የሚያስችለው የ"ሺልድ ቫክሲን" ማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክት ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ መድኃኒቶችን በጥራት ለመፈተሽ የሚያስችለው የባዮኢክዊቫለንስ ማዕከልም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አገልግሎቱን ለመጠቀም ፍላጎት ያሳዩበት ትልቅ አቅም ሆኗል።

May be an image of water heater

የምርምር ውጤቶችን ለሕዝብ ለማድረስ የሚዲያ ሚና የማይተካ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባለሙያዎች ቁጭትን ወደ አቅም በመቀየር፣ ዕድልን ወደ ድል በመለወጥና ሳይንሳዊ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ሕብረተሰቡን እንዲያነቁ ጥሪ አቅርበዋል።

በፎረሙ የተሳተፉት የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ የተቋሙን የሪፎርምና የፋርማሲዩቲካል ምርምር ሥራዎች በዘገባዎቻቸው ውስጥ በስፋት በማካተት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።