Search

በኦሮሚያ ክልል የገጠር አካባቢዎችን ለማዘመንና ልማትን ለማረጋገጥ የተነደፈው የ"ሃሮሜ" ስትራቴጂ እየተተገበረ ነው፡- ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

ሓሙስ ሰኔ 11, 2018 42

የኦሮሞ ሕዝብ የትግል ግቦች ስኬት የሚመሠረተው ከፖለቲካ ነፃነት ወደ ኢኮኖሚ ነፃነት በሚደረገው ሽግግር ላይ መሆኑንና ለዚህም የገጠርን ሽግግር እውን ማድረግ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

ክልሉ በአሁኑ ወቅት "ሃሮሜ" በተባለ ፕሮግራም ገጠርን የስደትና የልማት ዳርቻ ከመሆን አውጥቶ ወደ ዘመናዊ የልማት መሠረትነት እያሸጋገረው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

May be an image of campsiteርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፤ ኦሮሚያ በገጠር ላይ የተመሠረተ ክልል ቢሆንም፣ ለበርካታ ዓመታት ገጠር ያመረተው ምርት እሴት ሌላ ቦታ የሚከማች በመሆኑ ገጠር የልማት ዳርቻ ሆኖ ቆይቷል።

ይህ ልማዳዊ አሠራር ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት፣ ሥራ አጥነትንና የልማት ክፍተትን በማባባሱ፣ ለውጥ ለማምጣት በመጀመሪያ የገጠር ሽግግርን እውን ማድረግ የግድ ሆኗል።

No photo description available.

አቶ ሽመልስ የ"ሃሮሜ" ፕሮግራም የሕንጻ ግንባታ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የልማት አስተሳሰብ ለውጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዓላማው ገጠርን ከተማ ማስመስል ሳይሆን ዘመናዊነትን እስከ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ደጃፍ ማድረስ ነው ብለዋል።

በክልሉ ቀበሌዎች ሁሉ በፕላን በሚገነቡት በእነዚህ የገጠር ሽግግር ማዕከላት ውስጥ መንገዶች፣ ንጹሕ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ መስመር፣ ሶላር እና ባዮጋዝ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ጣቢያዎች፣ የመድኃኒት ቤቶችና ባንኮች፣ የፖሊስ ጣቢያዎች፣ ፍርድ ቤቶች፣ የገበያ ማዕከላት፣ መጋዘኖችና የንግድ ቤቶች፣ የሕፃናት መጫወቻ፣ የሕዝብ መሰብሰቢያና አረንጓዴ ቦታዎች እና የግብርና ማሽነሪዎች፣ የትራንስፖርት ማቆሚያዎችና የነዳጅ ማደያዎች አገልግሎቶች በውስጡ ያቀደ ነው።

በተጨማሪም የእያንዳንዱ አባወራ ግቢ የጓሮ አትክልት ልማትን፣ የዶሮና የወተት ላም እርባታን ያካተተ እንዲሆን እየተደረገ ሲሆን፣ ይህም ወጣቶች ባሉበት ቀያቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ዕድል ይፈጥራል።

ገጠርን የጥሬ ዕቃ ምንጭ ብቻ አድርጎ ከመመልከት መውጣት እንዳለበት ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ መሬት ከመቆፈርና ከማገድ ባለፈ አምራች፣ አቀነባባሪና ባለሀብት መሆን እንዳለባቸውና የእሴት ጭማሪ ሰንሰለት በገጠር መዘርጋት እንዳለበት ገልጸዋል።

በዚህ የሽግግር ጉዞ ውስጥ ከተማና ገጠር ተወዳዳሪዎች ሳይሆኑ አንዱ ለሌላው ዕድገት ቅድመ ሁኔታና መሠረት መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሽመልስ፤ ግንኙነታቸው የማምረት፣ የገበያ፣ የኢንቨስትመንትና የቴክኖሎጂ ትስስር መሆኑን አስገንዝበዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፤ "ለዓመታት ገጠር ተወላጆቹ የሚሰደዱበት ምድር ነበር፤ ዛሬ ግን የሚቆዩበት፣ የሚያመርቱበትና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን የሚገነቡበት እያደረግነው ነው" ብለዋል።

አክለውም የኦሮሞ ትግል ግቦች በከተሞች ብቻ እንደማይሳኩ በመጠቆም፣ "ገጠር ከተቀየረ ኦሮሚያ ይቀየራል፤ ገጠር ከተሻገረ ኦሮሚያ ይሻገራል" በማለት የ"ሃሮሜ" ፕሮግራም የክልሉን ሁለንተናዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ወሳኝ ስትራቴጂ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጠዋል።