Search

ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስኬት የሚረዱ ሁለቱ አስቻይ ሁኔታዎች

እሑድ ታኅሣሥ 12, 2018 45

የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስትራቴጂ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀጣዩን ምዕራፍ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂን ይፋ አድርገዋል።
ይህ አዲሱ ስትራቴጂ ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል ዕድል መፍጠር እንዲሁም በዜጎችና በተቋማት መካከል ያለውን መተማመን ማጎልበት የሚሉ ቁልፍ ትልሞችን አንግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስትራቴጂው ይፋዊ ማብሰሪያ ወቅት እንደገለጹት፤ እነዚህን ትልሞች እውን ለማድረግ የሕዝብ ዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል።
ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሰው ተኮር በሆነ መልኩ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም "የመደመር መንግሥት" ቢሮክራሲን በመቀነስ ታላላቅ ስትራቴጂዎችን እውን ለማድረግ ከያዘው ግብ ጋር የተቆራኘ መሆኑን አስረድተዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ግቦች እንዲሳኩ መሠረታዊ አስቻይ ሁኔታዎችን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመጀመሪያውና ዋነኛው የኤሌክትሪክ ተደራሽነት መሆኑን አብራርተዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ለዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት እንደምግብ መሆኑን በመጥቀስ፣ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች የኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈልጉ በመሆናቸው በሁሉም አማራጮች የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማስፋት ግድ እንደሚል አስገንዝበዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም የኢንተርኔት ትስስርን እንደ ሁለተኛው ወሳኝ አስቻይ ሁኔታ ያነሱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በርካታ ከተሞች የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቢሆኑም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ይህንን ትስስር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በስትራቴጂው ሰነድ ላይ እንደተመላከተው፤ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ዲጂታል መሠረተ ልማትና የሳይበር ደኅንነት ያሉት ግብዓቶች የስትራቴጂው መሠረታዊ "የዝግጁነት አቅሞች" ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ የዲጂታል ሕዝብ መሠረተ ልማት፣ መረጃ፣ ክህሎት፣ ፖሊሲና የቁጥጥር ማዕቀፎች ዝግጁነቱን ወደ ሚዛናዊ ለውጥ የሚቀይሩ "አነቃቂ ግብዓቶች" ተብለው ተለይተዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሮቦቶችንና ስማርት ማሽኖችን በሚጠቀመው "ኢንዱስትሪ 5.0" ቴክኖሎጂ የሚደገፍ ሲሆን፣ መንግሥት ለዚህ ስኬት ጥንቃቄ የተሞላበት ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ስትራቴጂው የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ ግቦችን በማስቀመጥ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያማከለ የዲጂታል ኢኮኖሚ ራእይን ለማረጋገጥ ይሠራል።
ይህ ስትራቴጂ የታለመውን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማሳካት የሚያስችሉ ዝርዝር የድርጊት መርሐ-ግብሮችና አተገባበሮችን የያዘ ሲሆን፣ ለዜጎች እኩል ዕድል የሚፈጥር ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ተመላክቷል።
 
በለሚ ታደሰ