Search

አካል ጉዳተኞች በሕዋ ጉዞ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ያስመሰከረችው ኢንጂነር

እሑድ ታኅሣሥ 12, 2018 44

ለስፖርት ልዩ ፍቅር ያላት ጀርመናዊቷ ኢንጂነር ሚካኤላ ቤንታውስ፣ ከሰባት ዓመታት በፊት በተራራ ላይ ብስክሌት እየጋለበች ሳለ በደረሰባት አደጋ በእግሯ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዳ ነበር።
ይህ አደጋ በተሽከርካሪ ወንበር እንድትንቀሳቀስ ቢያስገድዳትም፣ በልቧ ውስጥ የነበረውን ወደ ሕዋ የመጓዝ ትልቅ ህልም ግን ሊያደበዝዘው አልቻለም።
ኢንጂነር ሚካኤላ በአንድ ወቅት በ"ስፔስ ኤክስ" ኩባንያ ውስጥ ይሠራ የነበረና አሁን በጡረታ ላይ የሚገኘውን ሀንስ ኮይንግስማንን በበይነ-መረብ አንድ ጥያቄ ትጠይቀዋለች። ጥያቄውም "እንደ እኔ ያለ አካል ጉዳተኛ ጠፈርተኛ መሆን ይችላል?" የሚል ነበር።
የኢንጂነሯን ጽኑ ህልምና ፍላጎት የተረዳው ሀንስ ኮይንግስማን፣ በሕዋ ቱሪዝም ዘርፍ ወደሚሠራውና መቀመጫውን አሜሪካ ዋሽንግተን ወደአደረገው ብሉ ኦሪጂን የሕዋ ቴክኖሎጂ ኩባንያ እንድትሄድ ዕድሉን ያመቻችላታል።
ሀንስ ኮይንግስማን ለኢንጂነሯ "ምንም እንኳን የአካል ጉዳተኛ ብትሆኚም ወደ ሕዋ ከመጓዝ የሚገድብሽ ነገር የለም፤ ትችያለሽ!" በማለት አስፈላጊውን ምክር በመስጠት ህልሟን ለማሳካት ጥረቷን እንድትቀጥል አነሳስቷታል።
በአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ የምትሠራው ይህች ብርቱ ጀርመናዊት ኢንጂነር፣ ህልሟ ተሳክቶ ትላንት ከሌሎች አምስት ጠፈርተኞች ጋር በመሆን ለጥቂት ጊዜያት በሕዋ ላይ በመቆየት ምድርን ከላይ ለመመልከት ችላለች፤ ጉዞዋንም በስኬት አጠናቃ በሰላም ወደ መሬት ተመልሳለች።
ኢንጂነር ሚካኤላ በተሽከርካሪ ወንበር ሆና ወደ ሕዋ በመድረሷ ታላቅ ደስታ እንደተሰማት እና ከቡድኑ ጋር በመሆን በመስኮት ምድርን ስትመለከት እጅግ ስሜታዊ እንደነበረች ብሉ ኦሪጂን ያጋራው መረጃ ያመላክታል።
ኢንጂነሯ ፤ ለአካል ጉዳተኞች የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በማሟላት፣ ለሁሉም አካታችና አስቻይ ምህዳር መፍጠር ይገባል ስትል ጥሪዋን አቅርባለች። የእሷ የሕዋ ጉዞ የአካል ጉዳት ህልምን ከማሳካት የማያግድ መሆኑን ለዓለም ያሳየ ደማቅ ዐሻራ ነው ሲሉ በርካቶች ገልጸውታል።
 
በላሉ ኢታላ