ትውልዱ በዲጂታሉ ዓለም የሚኖረው ተሳትፎ ከፍ ያለ እንዲሆን ቢፈለግም የሀገርን ባህል በሚበርዝ መልኩ ሊሆን አይገባውም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ትልም እና ትግበራን በተመለከተ ባደረጉት የእሳት ዳር ወግ ላይ፤ ኢትዮጵያ ያላትን የዳታ ትራንዛክሽን መከላከል የሚያስችል ቁመና ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡
ይህንንም ከተለዋዋጩ ዓውድ ጋር ማስኬድ ካልተቻለ መልካቸውን ቀይረው ለሚሰነዘሩ ጥቃቶች ተጋላጭነት እንደሚፈጠር አመላክተዋል፡፡
በዚህም የሳይበር ደህንነት ተቋማት ሲስተም እና ዳታን ከጥቃት የመከላከል እንዲሁም ትውልድን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ትውልድን መጠበቅ ላይ በተለይም የትስስር መተግበሪያዎችን የሚጠቀሙ ዜጎች ቴክኖሎጂውን በምን መልኩ ሊጠቀሙ እንደሚገባ ማስተማር፣ መንገድ ሲስቱ መገሰፅ ወሳኝ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለቴክኖሎጂ የቀረበ ትውልድ ቢያስፈልገንም፤ የሀገርን ባህል በሚበርዝ መልኩ ግን አይደለም” ሲሉም አፅዕኖት ሰጥተዋል፡፡
በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች በርካቶች የሚከተሏቸው ተጽዖኖ ፈጣሪዎች ከተቀረው ዓለም የሚወስዱትን ትምህርት መምረጥ እና የሀገርን ባህል ይጣረሳል ወይ የሚለውን ማጤን እንደሚገባቸውም ነው የገለፁት፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ታዳጊዎች መተግበሪዎችን እንዳይጠቀሙ የከለከሉ ሀገራት ቢኖሩም እኛ ግን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው የተገነዘቡ ትውልድን መፍጠር ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
በአፎምያ ክበበው
#EBC #ebcdotstream #Digitalethiopia2030 #PMAbiy