Search

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው መስክ ምን ለመሥራት አቀደች?

ሰኞ ታኅሣሥ 13, 2018 37

የኢትዮጵያን የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ስኬታማ ለማድረግ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና አሻጋሪ ቴክኖሎጂዎች ዋነኛ የትኩረት መስክ መሆናቸውን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የነበረባትን ተከታይነት በመቀየር ወደፊት ለመስፈንጠር የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ማሽን ለርኒንግ፣ ሮቦቲክስ እና ብሎክ ቼይን ቴክኖሎጂዎችን በስፋት መጠቀም የግድ እንደሚላት ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
ስትራቴጂው የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በመንግሥት የሚመራ "የተደራጀ የክላውድ ሲስተም" (Sovereign Cloud) መገንባትን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፣ በ2030 መጨረሻ ላይም ኢትዮጵያ ከ60 ፔታባይት በላይ የሆነ መረጃን የመያዝ አቅም ያለው የክላውድ መሠረተ ልማት እንደሚኖራት አመላክተዋል።
የዳታ አስተዳደርን ለማዘመንና ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ዝግጁ ለማድረግም በ2030 ራሱን የቻለ ብሔራዊ የዳታ ባለሥልጣን እንደሚቋቋም ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ይፋ አድርገዋል።
በተጨማሪም የመሪዎችንና የተቋማትን የሥራ አፈጻጸም በየቀኑ በቀጥታ ለመከታተል የሚያስችል ሀገራዊ የዳታ ምዝገባ ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚሆንም ነው የገለጹት።
የመንግሥት አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው የመሶብ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በ23 ዘርፎችና ከ100 በላይ አገልግሎቶች ላይ ቢደርስም፣ በ2030 ግን ዜጎች በአካል ሳይገኙ በቤታቸው ሆነው ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ አገልግሎት የሚያገኙበት የተቀናጀ ፕላትፎርም እንደሚዘረጋም አመላክተዋል።
ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር በአገልግሎት ዘርፍ የሚታየውን የሌብነትና የሙስና ችግር በሥርዓት ለመፍታትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።
 
በለሚ ታደሰ