በሰው-ማሽን ትብብር (Cobots) የሚደገፈው ‘ኢንዱስትሪ 5.0’ የቀጣዩን ዘመን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚወስን ነው።
በ’ኢንዱስትሪ 5.0’ አውድ፣ ኮቦት (cobot) ትኩረቱን ከሙሉ አውቶሜሽን ወደ ሰው-ማሽን ትብብር ለመቀየር የሚያገለግል ዋና መሣሪያ ነው።
ዘመኑ እያለፈ ያለው ‘ኢንዱስትሪ 4.0’ ትኩረት ያደረገው ስማርት ኢንዱስትሪዎች ላይ ነበር። የቀጣዩን ዘመን መሪነት የሚረከበው ‘ኢንዱስትሪ 5.0’ ደግሞ እጅግ የረቀቀ እና ሰውን ያማከለ ሆኖ የሰው እና ማሽኖች ትሥሥር ውጤታማ (efficient) የሚሆንበት እንደሆነ ይነገራል።
ሰውን ማዕከል ማድረግ፣ ዘላቂነት እና ቀጣይነት የሚሉ ሦስት ዋና ምሰሶዎቹ ሲሆኑ፣ ለሠራተኞች ደኅንነት፣ ጤንነት እና የፈጠራ አስተዋፅዖ ቅድሚያ ይሰጣል።
ሰዎችን ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ማላመድን ከሚጠይቀው ያለፈው ዘመን ኢንዱስትሪ በተለየ ቴክኖሎጂ ለሰዎች ምን ሊያደርግ እንደሚችል የሚወስንም ነው።
ብክነትን የሚቀንሱ፣ ታዳሽ ኃይልን የሚጠቀሙ እና ከአጭር ጊዜ ትርፍ ይልቅ የምድርን የረዥም ጊዜ ጤናማነት እና ምርታማነት ላይ የሚያተኩሩ የምርት ሂደቶችን ይነድፋል።
እንደ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓይነት አስጊ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ የምርት እና አገልግሎት የአቅርቦት ሰንሰለት ቀውሶች እንዳይፈጠሩም መንገድ ያበጃል።
‘ኢንዱስትሪ 5.0’ ያልታሰቡ ክስተቶች ሲፈጠሩ በፍጥነት መላመድ እና ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ ለሚያስችሉ የግንባታ ሥርዓቶች አፅንዖት ይሰጣል።
‘ኢንዱስትሪ 5.0’፣ ‘ኢንዱስትሪ 4.0’ን አጥፍቶ የሚተካው ሳይሆን ከዘመን ጋር እንዲራመድ በሚያስችለው መንገድ (Augmenting) ተጨማሪ አቅም የሚሆንለት ነው።
ለደኅንነት ሲባል ከሰዎች ጋር ያላቸው መስተጋብር ውስን በነበሩት ሮቦቶች (Robots) ከሚታገዘው ነባር ኢንዱስትሪ በተለየ፣ ከሰዎች ጋር በመቀናጀት በሚሠሩ ኮቦቶች (Collaborative Robots/Cobots) የሚታገዝ እና ተደጋጋሚ ሂደቶችን በማስቀረት ለሰው ልጆች የተሻለ ዓለምን የሚፈጥር ነው።
ፍጥነትን በመጨመር እና ብክነት በመቀነስ የቢሆን አስተሳሰብን አስቀርቶ በተግባር ምርትማነትን የሚያሳድግ እንደሆነም ይነገርለታል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሁሉንም ውሳኔዎች አንዲወስን የሚተው ሳይሆን፣ በመረጃ ላይ የተመሠረቱ አማራጮችን ለሰዎች የሚሰጥ ነው።
አካላዊ ውጥረትን ለማስቀረት እንደ "exoskeletons" ባሉ መሣሪያዎች በመጠቀም ውስብስብ ጉዳዮችን ያቀልላል። ለቴክኒሻኖች የእውነተኛ ጊዜ መመሪያዎችን በሚሰጡ የረቀቁ መሣሪያዎች (Augmented Reality) ይታገዛል።
እንደ ቢኤም ደብሊው እና አውዲ ያሉ የመኪና ፈብሪካዎች ኮቦት (Cobots) በመጠቀም ከባድ የመኪና አካላትን እየገጣጠሙ ይገኛሉ። በዚህም ከፍተኛ ፍጥነት እና ቅልጥፍናን በመጨመር የሠራተኞቻቸውን የረጅም ጊዜ ጉዳት እየቀነሰ የምርት ጥራታቸውን እያሳደገ ይገኛል።
ኮቦት (Cobots) በፋሽን ኢንዱስትሪውም ሥራ ላይ ውሎ ውጤት እያሰመዘገበ ይገኛል። የፋሽን ኢንዱስትሪዎች በአንድ ጊዜ በሺህዎች የሚቆጠሩ ትዕዛዞችን ተቀብለው ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ከሰዎች ጋር በማጣመር በ24 ሰዓታት ውስጥ እያደረሱ ይገኛሉ።
የምግብ ፋብሪካዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የንጥረ ነገሮችን አጠቃቀምን እና ምጣኔ የማስተካከል ሥራዎችን እየሠሩ ሲሆን፣ ይህም የኬሚካል ብክነትን እና የኃይል ፍጆታን በእጅጉ እየቀነሰ ይገኛል።
እየተጠናቀቀ ያለው የፈረንጆች ዓመት (2025) ለ‘ኢንዱስትሪ 5.0’ መሠረት መጣል ቅድሚያ የሰጡ ኩባንያዎች ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ረገድ የበለጠ ስኬታማ መሆናቸውን ያረጋገጡበት ዓመት ነው።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 እና ‘ኢንዱስትሪ 5.0’
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ላይ እንደተቀመጠው ኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እንድታሳካ ‘ኢንዱስትሪ 5.0’ ሂደቱን የማሳለጥ አቅም የሚፈጥር ነው።
ዓላማውን ለማሳካትም ለዲጂታል ሉዓላዊነት እና ለሀገር ውስጥ ፈጠራ ዕድል ቅድሚያ የሚሰጥ ሲሆን፣ ለሚዛናዊ ዓለም አቀፍ ሽርክናዎችም ቦታ ይሰጣል።
ለሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የማሽን መማሪያ (Machine Learning /ML/)፣ በይነመረብ (IoT)፣ ‘ክላውድ’፣ ‘ብሎክቼይን’/ያልተማከለ የመረጃ ሥርጭት ቴክኖሎጂ (DLT)፣ ‘ኳንተም ኮምፒዩቲንግ’፣ ሮቦቲክስ (Robotics) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ያሳካሉ ተብለው ቅድሚያ የተሰጣቸው ቁልፍ ቴክኖሎጂዎች ናቸው።
አስተማማኝ ኃይል እና ብሮድባንድ ኢንገተርኔት ለ‘ኢንዱስትሪ 5.0’ ስኬት ወሳኞች ሲሆኑ፣ ጠንካራ የሳይበር ደኅንነት ደግሞ ብሐራዊ ጥቅምን ለመጠበቅ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራ ነው።
አሁን የተጀመሩት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ፣ የተዋሃዱ ክፍያዎች ሥርዓት፣ ብሔራዊ የመረጃ ልውውጥ፣ ኢ-አገልግሎት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተሳኩ ሲሆኑ፣ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ደግሞ መሠረት የጣሉ ናቸው።
ከሁሉም በላይ ለዚህ መፃኢ ኢንዱስትሪ ዝግጁ የሆነ የሰው ኃይል ማዘጋጀት በጣም አስፈላጊ ጉዳይ በመሆኑ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች የማዘጋጀት ሥራ አየተሠራ ይገኛል።
ግብርና፣ ጤና፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ትምህርት፣ ፋይናንስ፣ ቱሪዝም እና ቅርስ፣ የአየር ንብረት እና የከተማ ልማት፣ ትራንስፖርት፣ ሎጂስትክስ፣ ንግድ እና የፈጠራ ኢንዱስትሪዎች ‘ኢንዱስትሪ 5.0’ ተግባራዊ የሚደረግባቸው ዘርፎች ናቸው።
በለሚ ታደሰ
#EBC #EBCdotstream #dijitalethiopia #robots