ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስራን በፍጥነት በማከናወን በአሁን ወቅት ዓለማችንን በከፍተኛ ፍጥነት እየለወጠ የሚገኝ ቴክኖሎጂ ነው፡፡
ይህ የፈጠራ ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመነ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በመዋል ውጤታማ የሆኑ ተግባራትን ማከናወን ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡
ኤ አይ በጤና ጥበቃ፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርት፣ በግብርና እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች ላይ አሻራውን በማሳረፍ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በግብርናው ዘርፍ ትክክለኛ ግብርና (Precision Agriculture) የተሰኘ አዲስ የአሰራር ዘይቤን እየፈጠረ ነው፡፡

ይህ ዘይቤ አርሶ አደሮች አነስተኛ ግብአት ተጠቅመው ከፍተኛ የሆነ ምርት መሰብሰብ የሚያስችል ነው፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት በግብርናው ዘርፍ ላይ እያበረከተ ከሚገኘው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች መካከል የሰብል ጤንነትን መጠበቅ እና የተባይ ቁጥርን መቀነስ አንደኛው ነው። የሰው ሰራሽ አስተውሎትን የሚጠቀሙ ካሜራዎች እና ድሮኖችን ማሳው ላይ በማብረር የሰብሉን ሁኔታ በመቃኘት መረጃ መሰብሰብ ያስችላል፡፡
ኤ አይ ሰብሉ ገና መታመም ሲጀምር በቅጠሉ ቅርፅ እና ቀለም በሽታን የመለየት ተግባር ያከናውናል፡፡

ኤ አይ ተባይ ያለበትን ቦታ በትክክል በመለየት ኬሚካልን በጅምላ ሁሉንም ከመርጨት ይልቅ ተባዩ ያጠቃበት ቦታ ላይ ብቻ እንዲረጭ ያደርጋል፡፡
የአፈር ምርመራ እና ማዳበሪያ አጠቃቀምን በተመለከተ አፈር ውስጥ የሚገኘውን እርጥበት የናትሮጂን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን በመለካት እያንዳንዱ ተክል ምን ያህል ውሃ እና ማዳበሪያ እንደሚያስፈልገው በማሳወቅ ብክነትን ማስቀረት ያስችላል፡፡
በመዝራት እና በማረም ሒደት ውስጥም ኤ አይ በተለያዩ ሀገራት ጉድ የሚያሰኙ ተግባራቶችን በማከናወን ላይ ነው፡፡

ለምሳሌ በቻይና በኤ አይ የሚመሩ ሮቦቶች፣ ሰው አልባ ትራክተሮች እና ማሽኖች የግብርናውን ስራ እያቀለሉት ይገኛሉ፡፡
በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚመሩት ሮቦቶች ዘሮችን በትክክለኛ ርቀት ይዘራሉ፣ እንዲሁም ሰብሉን ሳይነኩ አረምን ብቻ ለቅመው ያርማሉ፡፡ እነዚህ ሮቦቶች መዝራት እና ማረም ብቻ ሳሆን ምርት መሰብሰብ ላይም ይሳተፋሉ፡፡
ፍራፍሬዎች መብሰል እና አለመብሰላቸውን ለይተው የሚለቅሙ ሮቦቶች አሁን ላይ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚመሩት ሮቦቶች እንደ ሰው የማይደክሙ እና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ስራቸውን የሚያከናውኑ በመሆናቸው ዓለም በስፋት እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡ የቻይና ግብርና የሰው ሀይል እጥረት እየገጠመው እንደነበር የሚወጡ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚመሩ ትራክተሮች ወደ ግብርናው መቀላቀላቸው የተፈጠረውን የሰው እጥረት በመተካት የግብርና ስርዓቱን በማዘመን ሰፊ ስራ ማከናወን ማስቻሉን መረጃው አካቷል፡፡

ትራክተሮቹ ጉልበት ቆጣቢ ከመሆናቸው ባሻገር 20 ፐርሰንት የሚሆን የምርት ጭማሪንም ማስመዝገብ ችለዋል፤ ይህም በምርቶች ላይ የሚከሰተውን ብክነት ማስቀረት አስችሏል፡፡
የቻይና መንግሥት በ2030 ለማሳካት ካስቀመጣቸው ግቦቹ መካከል ከሚታረሰው የሀገሪቷ መሬት 50 ፐርሰንቱን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በሚመሩ ትራክተሮች ለማከናወን አቅዶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የምግብ አቅርቦት ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት እና ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሌሎች ሀገራት የቻይናን ተሞክሮ በመጋራት የሰው ሀይል እና ቴክኖሎጂዎቹን ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ ለመጠቀም ፍላጎት አሳድረዋል ፡፡
በኢትዮጵያም ግብርናውን ለማዘመን ኤ አይን ተግባራዊ በማድረግ ለውጥ ማምታጣት ተችሏል፡፡

እንደ አሜሪካ ወይም ቻይና ያሉ ሀገሮች ግዙፍ ሰው አልባ ትራክተሮችን መጠቀም ባንችልም ለኢትዮጵያውያን አውድ የሚሆኑ መፍትሔዎችን መጠቀም ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያን ግብርና ውጤታማ ለማድረግ በኤ አ ይ አማካኝነት በመከናወን ላይ ከሚገኙ ተግባራት መካከል አብዛኛው የኢትዮጵያ አርሶ አደር ስማርት ስልክ ተጠቃሚ ባይሆንም በቤተሰቡ ውስጥ ያሉ ወጣት ልጆች ስልኮችን በመጠቀም የኤ አይ አሰራርን ተደራሽ ማድረግ አስችሏል፡፡
አንድ ገበሬ የታመመ የሰብል ቅጠሎችን ፎቶ በማንሳት በኤ አይ መተግበሪያ ለምሳሌ እንደ (Plant Village Nuru) አማካኝነት በሽታውን እና መድሐኒቱን በሰከንዶች ውስጥ መለየት እና ማወቅ ይችላል፡፡

ይህ አሰራር በኢትዮጵያ ስንዴና ቡና ላይ እየተሞከረ ያለ ዘዴ ነው።
በሌላ መልኩ አርሶ አደሩ በአፍ መፍቻ ቋንቋው የሚያስፈልገውን መረጃ ጠይቆ በኤ አይ አማካኝነት የግብርና ምክሮችን ማግኘት የሚችልበት አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚበሩ ድሮኖችን በሰብሉ ላይ በማሰማራት ውሀ ያጠረውን አካባቢ፣ በበሽታ የተጠቃውን እንዲሁም ሌሎችንም ችግሮች ለይተው መረጃ የሚሰጡ አሰራሮችም መተግበር ያስችላል፡፡
የአየር ንብረት ትንበያን በተመለከተ ኤ አይ ያለፉ ዓመታትን መረጃዎች በመተንተን የዝናብ ወቅትን ዝናብ መጠኑን እና ድርቅን የመተንበይ አቅም አለው፡፡
ይህም መረጃን በመተንተን ገበሬው መቼ መዝራት እና ምርትን መሰብሰብ እንዳለበት መረጃ ይሰጣል፡፡
የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በብዛት በገጠራማው የሀገሪቷ ክፍል የሚኖሩ እና የኢንተርኔት ተደራሽነቱም ገና እየተስፋፋ የሚገኝ በመሆኑ ተግዳሮቶች ቢኖሩም መንግሥት ኤ አይ ለኢትዮጵያ ግብርና ዘመናዊነትን ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚረዳ ትልቅ አቅም መሆኑን በማመን ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ