ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የኢትዮጵያን የክፍያ ሥርዓት ከመሰረቱ ቀይሮታል ሲሉ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር) ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
በተለይ የቴሌብር መምጣት የክፍያ ሥርዓቱን መቀየሩን ያወሱት አማካሪው፤ አሁን ላይ ከ54 ሚሊዮን በላይ ዲጂታል ክፍያ የሚፈፀምባቸው አካውንቶች አሉ ብለዋል።
በፈረንጆቹ 2030 ዲጂታል ክፍያን ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት አንጻር አሁን ካለበት ከ7 እጥፍ በላይ ለማሳደግ በልዩ ትኩረት ይሠራል ያሉት ደግሞ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ናቸው።
የኢንተርኔት ትስስር ለዲጂታል አገልግሎቶች መሠረት በመሆኑም፤ ከ5 ዓመት በፊት17 ሚሊዮን የነበረውን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር 57 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ዮዳሄ አርዓያሥላሴ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተመዝጋቢዎች ቁጥር ከ30 ሚሊዮን በላይ ደርሷል ያሉ ሲሆን፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ፋይዳን ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ አመላክተዋል።
በስትራቴጂው የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካትም እስከ ታችኛው መዋቅር ያሉ አገልግሎቶችን ከፋይዳ ጋር የማስተሳሰር ሥራ በትኩረት እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጅ ተቀርጾ ተግባራዊ መደረጉ ሁሉንም ሴክተሮች አቀናጅቶ ውጤታማ ሥራ በማከናወን ዲጂታል ኢኮኖሚን ከመገንባት አኳያ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የተቀመጡ ግቦች እንዲሳኩ በሁሉም አማራጮች የኃይል ትስስርን ማስፋት እና በሁሉም አካባቢዎች የኢንተርኔት ተደራሽነትን ማረጋገጥ ማድረግ ይገባል ማለታቸውም አይዘነጋም።
በየተመኙሽ አያሌው
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #DigitalEthiopia #DigitalFinance