Search

የምድር ፈተናዎች እና በሰው ልጅ የተዘነጉ ጥፋቶች

ሓሙስ ታኅሣሥ 16, 2018 270

በሳይንሱ ዓለም የምድር ጥፋቶች ተብለው የሚታወቁ ዋና ዋና ጉዳዮች መነሻቸው የሰው ልጅ መሆኑን ለተረዳ ለምን ብሎ ቢጠይቅ መልሱ አንድ ነው። የሰው ልጅ በምድር ላይ ያለው የማይቆም ፍላጎት እና ሃላፊነትን አለመውሰድ ዋናው ችግር ሆኖ ይታወሳል።

በቡድን ተቧድኖ ትልቁን ፍጥረት ከማጥፋት እስከ ዓለም አቀፋዊ ቀውስ ከዳረገው ጦርነት ጀምሮ አሁን የዓለም ፈተና እስከሆነው የዓየር ንብረት ለውጥ ምድርን ሲኦል እያደርጓት መሆኑ አያጠያይቅም። ለዚህም ነው ምድራችን እየተገባደደ እስካለው የፈረንጆች ዓመት ድረስ አፋጣኝ እርምጃ ከሚጠይቁ በርካታ አንገብጋቢ ችግሮች ጋር እየታገለች ያለችው። የችግሮቹ ዋና ምክንያት ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች በብዝኃ ሕይወት ላይ የደቀነው አደጋ ዓለምን ለሰው ልጆች ሲዖል እስከማድረግ ግልጽ አደጋዎች ያስከትሉ እና አስቸኳይ እርምጃዎችን የሚጠይቁ ናቸው። እነዚህ አደጋዎች ዛሬም የሰው ልጅን መፍትሄ የሚሹ በመሆኑ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ተስፋን የሚጠብቁ ናቸው። ጥቂቶቹን እንመልከታቸው፦

1.     የምግብ ብክነት

ዓለም ላይ በምግብ እጥረት ምክንያት የብዙ ዜጎች ሕይወት ማለፍ ዓለም ያልተሻገረችው ዛሬም ከዋና ችግሮቿ አንዱ ነው። የተቃርኖ ዓለም በምትመስለው ምድራችን ምግብ ሞልቶ እንደሚደፋባት ሁሉ የምግብ ሽታ የናፈቃቸው ዜጎች በሚሊዮን ቁጥር የሚቆጠሩ ናቸው።

ኧርዝ ዶት ኦርግ ላይ የወጣው ጥናት እንዳመላከተው ለሰው ልጅ ፍጆታ ከሚውለው ምግብ ውስጥ አንድ ሦስተኛው ወይም ወደ 1.3 ቢሊዮን ቶን የሚሆነው ይባክናል፡፡ ይህ የምግብ መጠን 3 ቢሊዮን ሰዎችን ለመመገብ በቂ ነው፡፡ ይህ የሚባክነው (የሚጣለው) የምግብ መጠን ለሰዎች ምግብ ሳይሆን ከመቅረቱም በተጨማሪ ደግሞ በየዓመቱ ለሚከሰተው የአየር ብክለት የአንድ አራተኛው የግሪንሃውስ ጋዝ ልቀት ምክንያት ሆኗል። አንድ ችግር ሁለት መከራን ለምድር ያመጣ ሆኖ በ2025 መፍትሄን የሚሻ ሆኗል።

2.    የብዝኃ ሕይወት መጥፋት

ባለፉት 50 ዓመታት የሕዝብ ብዛት፣ የሰው ልጅ ፍጆታ፣ የንግድ እና የከተሞች መስፋፋት ፈጣን እድገት አሳይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የሰው ልጅ ተመልሶ ሊያገግም ከሚችለው በላይ የምድርን ሃብት አሟጥጦ ተጠቅሟል። ይህ ደግሞ ከ500 በላይ የምድር ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ሲሆን፣ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ውስጥ ካለፈው ምዕተ-ዓመት ተመሳሳይ መጠን ያላቸው የሥነ-ሕይወት ዝርያዎች ሊጠፉ ይችላሉ፡፡ ሰዎች የምድር ሃብትን በጥንቃቄ ወደ መጠቀም እና የተበላሹትን ወደ ማካም ካልተመለሱ ፕላኔታችን የማትመለስበት አደጋ ውስጥ እንደምትገባ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ተመራማሪዎች እንደሚሉት እነዚህ ዝርያዎች የሰው ልጅ እጅ ባይኖርባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ይቆዩ ነበር።

3.    የፕላስቲክ ብክለት

በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ ወደ 14 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ የፕላስቲክ ምርቶች ወደ ውቅያኖሶች እየገባ ነው፡፡ ይህም የባሕር ውስጥ ብዝኃ ሕይወትን፣ የዱር አራዊት መኖሪያዎችን እና አጠቃላይ የባሕር ሥነ-ምህዳርን እየጎዳ ይገኛል።

ምንም ዓይነት እርምጃ ካልተወሰደ በ2040 የፕላስቲክ ብክለት በዓመት ወደ 29 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚያድግ ጥናቶች አረጋግጠዋል። ማይክሮፕላስቲኮች እዚህ ውስጥ ከተካተቱ ደግሞ ወደ ውቅያኖስ የሚገባው የፕላስቲክ መጠን ወደ 600 ሚሊዮን ቶን ሊደርስ ይችላል። አሁን ያለው አካሄድ ሳይታረም ከቀጠለም የባሕር ሥነ-ምህዳር ሙሉ በሙሉ ስለሚበላሽ ምድር ወደማትወጣው ቀውስ እና ከፍተኛ ሙቀት ትገባለች ይላሉ በዚህ ዙሪያ የወጡ ጥናቶች፡፡

4.   የደን ጭፍጨፋ

በዓለም ላይ በየሰዓቱ 300 የእግር ኳስ ሜዳዎችን የሚያክል ደን ይጨፈጨፋል። ይህ ሂደት እንደዚህ ከቀጠለ በአውሮፓውያኑ 2030 ፕላኔታችን 10 በመቶ ደን ብቻ ሊቀራት ይችላል፡፡ የደን ጭፍጨፋው መፍትሔ ካልተበጀለት ደግሞ ከመቶ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መሬት አንድም ዛፍ የማይታይባት ምድረበዳ ልትሆን እንደምትችል ጥናቶች ያመላክታሉ። ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ ከሚካሄድባቸው ቀዳሚ ሀገራት ሦስቱ ብራዚል፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኢንዶኔዥያ ናቸው። ግብርና ደግሞ ለደን ጭፍጨፋ ዋነኛው መንስኤ ነው። እዚህ ላይ ዓለማችን እንደኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ አይነት መፍትሔዎችን ካልተከተለች ለሰው ልጅ መኖሪያነቷ አደጋ ውስጥ ይወድቃል።  

5.    የአየር ብክለት

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ከ4.2 እስከ 7 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች በአየር ብክለት ምክንያት ይሞታሉ። ከአሥር ሰዎች ዘጠኙ ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ብክለት የያዘ አየር ይተነፍሳሉ። በቅርቡ የተካሄደው የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ጨምሮ በርካታ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚካሄዱ ውይይቶች ቢኖሩም ለዚህ ጉዳይ ያመጡት መፍትሔ የችግሩን ያክል አይደለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ለመፍትሔው እየሠሩ ቢሆንም ዓለም ከቃል ባለፈ በተጨባጭ ተግባር ካልተባበረ ምድር ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖባታል፡፡

6.   የበረዶ መቅለጥ እና የባሕር ከፍታ መጨመር

እየጨመረ ባለው የሙቀት መጠን ምክንያት የባሕር ከፍታ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበረው ከእጥፍ በላይ እየጨመረ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የባሕር ከፍታ በዓመት በአማካይ 3.2 ሚሊ ሜትር እያደገ ሲሆን መፍትሔ ካልተበጀለት በዚህ ክፍለ ዘመን መጨረሻ እስከ 0.7 ሜትር ገደማ ከፍ ማለቱን ይቀጥላል፡፡ እንደ ተመራማሪዎች ገለጻ የባሕር ከፍታ መጨመር እንዲሁ ከቀጠለ ከ340 እስከ 480 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የሚኖሩባቸውን የባህር ዳርቻዎች ይጥለቀለቃሉ፡፡ ይህ ደግሞ የዚህ አካባቢ ነዋሪዎች ደኅንነታቸው ወደ ተጠበቁ አካባቢዎች እንዲሰደዱ እና በሚሰደዱባቸው አካባቢዎች ለሕዝብ ብዛት እና መጨናነቅ ምክንያት ይሆናል።  

7.    የውቅያኖስ አሲዳመነት መጨመር

የዓለም ሙቀት መጨመር ለውቅያኖስ አሲዳማነት በመጨመርም ዋነኛ መንስኤ ነው፡፡ ውቅያኖሶች ወደ ምድር ከባቢ ከሚለቀቀው ካርቦንዳይኦክሳይድ 30 በመቶ ያህሉን ይስባሉ። ሳይንቲስቶች ከፍተኛ ብዝኃ ሕይወት የያዘው የባሕር ወለል (coral reef) በ2050 ሙሉ በሙሉ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል እያሉ ነው። ይህ ደግሞ በውቅያኖሶች ውስጥ ያለው ብዝኃ ሕይወት ላይ ከፍተኛ አደጋን የጋረጠ ሆኗል።

8.    ግብርና

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓለም የምግብ ሥርዓት የሚመጣው የግሪንሃውስ ጋዝ ልቀት ከፍተኛው ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 30 በመቶ የሚሆነው የሚከሰተው በእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ነው። የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ጥቅም ላይ የሚውለው ማዳበሪያ ደግሞ እንደ ናይትረስ ኦክሳይድ ያሉ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ወደ ከባቢ የሚለቅቁ ናቸው። 60 በመቶ የሚሆነው የዓለም ግብርና በእንስሳት እርባታ የተያዘ እና ለብክለቱም ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ቢሆንም፣ ለዓለም አቀፍ የሥጋ ፍላጎት አቅርቦት ያለው አስተዋጽኦ ግን 24 በመቶ ብቻ ነው። ታዲያ የተለመደው የግብርና ዘዴ መቀየር የማይችል ከሆነ ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ ምድር ባዶዋን እንደምትቀር ነው ሳይንቲስቶች እያስጠነቀቁ ያሉት፡፡

9.   የአፈር መሸርሸር

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት 40 በመቶ የሚሆነው የፕላኔቷ አፈር ታጥቧል። ባህላዊ የግብርና ዘዴዎች እና ለምርት መጨመር ጥቅም ላይ የሚውሉ መርዛማ ኬሚካሎች ለአፈር መሸርሸር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ እስከ 2050 ድረስ ከቀጠለ፣ ደቡብ አሜሪካን የሚያክል አካባቢ ለተጨማሪ የአፈር መሸርሸር እንደሚጋለጥ በጥናቶች ተረጋግጧል። ሁኔታዎች እንደተለመዱት ከቀጠሉ በ20 ዓመታት ውስጥ ወደ 9.3 ቢሊዮን ከፍ ይላል ተብሎ ለሚታሰበው የዓለም ሕዝብ መሬት ልታቀርበው የምትችለው ምግብ ከ40 በመቶ በታች ይሆናል፡፡

10.  የፋሽን እና የጨርቃጨርቅ ተረፈ ምርት

እንደ ተመድ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም መረጃ የፋሽን ኢንደስትሪው 10 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የካባቢ ብክለት ድርሻ ይይዛል፡፡ የፋሽን አንዱስትሪ ብቻውን አቪዬሽን እና የባሕር ትራንስፖርት ዘርፎች ከሚፈጥሩት በ20 በመቶ የበለጠ የብክለት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው፡፡ የጨርቃ ጨርቅ እና ማቅለሚያ ፋብሪካዎች 93 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ቆሻሻ ወደ ከባቢ ይለቅቃሉ።

11.    የኮባልት ማዕድን

ለኤሌክትሪክ ባትሪ ምርት ዋነኛ ማዕድን የሆነው ኮባልት ወደ ታዳሽ ኃይል ለሚደረገው ሽግግር ወሳኝ ቢሆንም በማውጣቱ ሂደት የሚፈጠረው ብክለት ግን አወዛጋቢ እየሆነ ነው። ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ የኮባልት ማዕድን የማውጣት ሂደት ከመኖሪያ አካባቢ ውድመት እስከ የውኃ እና የአየር ብክለት ድረስ ከፍተኛ የአካባቢ ተፅእኖዎች አሉት።

የዓለማችን ትልቋ የኮባልት አቅራቢ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ስትሆን፣ አንድ አምስተኛው የሚሆነው የሚመረተው በባህላዊ ማዕድን አውጪዎች ነው ተብሎ ይገመታል። የዚህ ዓይነቱ ባህላዊ የኮባልት ማዕድን ማውጣት ደግሞ ከአካባቢ ተፅዕኖ በተጨማሪ አደገኛ የሰው ጉልበት ብዝበዛ እና ሌሎች ከባድ የአካባቢ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ጋር የተቆራኘ ነው።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደቡባዊ ክልል የኮባልት እና የመዳብ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ዩራኒየም መገኛ ስለሆነ አካባቢው ራዲዮአክቲቭ እየተስዋለበት መሆኑንም ሳይንቲስቶች እየገለጹ ነው። በተጨማሪም ከእነዚህ አካባቢዎች የመወጣው ኬሚካል ወደ አጎራባች ወንዞች እና የውኃ ምንጮች እየገባ ብክለት እየፈጠረ መሆኑን ዓለም አቀፍ የአካባቢ እና ልማት ተቋም (iied) ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአጠቃላይ ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት የቀረው የፈረንጆች 2025 ምድራችን በርካታ ውስብስብ ችግሮችን ያስተናገደችበት ዓመት ነው፡፡ ለበርካታ ችግሮች የመፍትሔ ቢቀርቡም፤ ለመፍትሔውም በርካቶች ቃል ቢገቡም ቃል እና ተግባር እየተገናኙ ስላልሆነ ምድር ችግሯቹን አዝላ ቀጥላለች፡፡ በተለይም በኢኮኖሚ የበለፀጉ ሀገራት ለጊዜው የችግሮቹ ስሜቶች ስለማይነኳቸው ለመፍትሔ ያላቸው ጥድፊያ አናሳ መሆኑ የፕላኔቷ ችግሮች ውስብስብ ሆነው እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡ ቀጣዩ ጊዜስ ሰዎች ልቦና ገዝተው የምድርን ፈተና የሚያቃልል ሥራ ይሠሩ ይሆን ወይስ ባሉት ችግሮች ላይ እየደራረቡ ወደ ፍጻሜዋ ያደርሷት ይሆን?

በለሚ ታደሰ