ታዋቂው የስዊዝ ሰዓት አምራቹ ኩባንያ ሮሌክስ የሚያገኘውን ዳጎስ ያለ ትርፍ ወደ ኪሴ ሳይል መቶ በመቶ ለበጎ አድራጎት ድርጅትይለግሳል፡፡
ኩባንያው በዓመት ከ1 ሚሊዮን 200 ሺህ በላይ የእጅ ሰዓቶችን የሚያመርት ሲሆን፣ ለዓመታት ይዞት በቆየው ጥራትም ትላልቅ የሀገራት መሪዎች፣ የዓለማችን ዝነኛና ታዋቂ ሰዎች የሚመርጡት ሰዓት ሆኗል።
እ አ አ በ1905 የተቋቋመው ይህ የስዊዝ ሰዓት አምራች ኩባንያ፣ ባሳለፍነው ዓመት ብቻ ከ10 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ሽያጭ ያከናወነ ሲሆን፣ ከዚህም የተገኘውን ትርፍ ሙሉውን ለበጎ አድራጎት ድርጅት ለግሷል።
ምክንያቱም የሮሌክስ ኩባንያ ቁጥር አንድ ሕግ፣ በየዓመቱ የሚያገኘውን ትርፍ መቶ በመቶ ለበጎ አድራጎት ድርጅት እንዲሰጥ ስለሚያዝ ነው።
የዚህ ኩባንያ መስራች ባለቤት ሃንስ ዊልስዶርፍ ይባላል፡፡ በልጅነቱ ቤተሰቦቹን በሞት በማጣቱ ምክንያት የአዳጊነት እድሜውን በአዳሪ ትምህርት ቤት አጠናቅቋል፡፡
ከዚያም በኋላ በስዊዘርላንድ ውስጥ በሚገኝ ታዋቂ የሰዓት ማምረቻ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ የሰራ ሲሆን ልክ በ24 ዓመቱ የዛሬውን ግዙፍ ኩባንያ ሮሌክስን አቋቋመ።
ይህ ኩባንያ እንደተመሰረተም በምርቱ ጥራት በዓለም ዙሪያ ተቀባይነት ማግኘት ጀመረ፡፡ ሮሌክስ የሚባለው ስያሜ የቅንጦትና የዘመናዊ ሰዓት ስም እስኪሆን ድረስ ተወዳጅና ተመራጭ ምርት እየሆነ መጣ።
ዊልስዶርፍ ኩባንያውን ለታላቅ ስኬት ካበቃ በኋላ በ79 ዓመቱ እአአ በ1960 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
ባለቤቱ ከሱ ቀድማ ሕይወቷ በማለፉ እና ከአብራኩ የተገኙ ልጆች ስላልነበሩት፣ ዊልስዶርፍ መመሞቱ በፊት የሮሌክስ ኩባንያ ትርፍ ሙሉ በሙሉ ዊልስዶርፍ ለሚባለው በስሙ ለተቋቋመው የበጎ አድራጎት ድርጅት እንዲሰጥ ተናዞ ነበር።
በዚህም ምክንያት ኑዛዜው በሕግ ተጠብቆ እስከዛሬ ድረስ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ በዚህም በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር የሮሌክስ ኩባንያ የተጣራ ትርፍ ለትምህርት፣ ለአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም ለሳይንሳዊ ምርምር በተለይም ለትምህርት ማስኬጃ እንዲውል በዊስዶርፍ ፋውንዴሽን አማካኝነት ይሰጣል።
ባለፈው ዓመት ኩባንያው ካገኘው ከ2 ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ የተጣራ ትርፍን መቶ በመቶው በዚህ መልኩ ተሰጥቷል።
ሚሊዮን ዶላሮች ከሚያወጡ የቅንጦት ሰዓቶች ጀምሮ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለመደበኛ ተጠቃሚውም የሚያመርተው ሮሌክስ፣ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት አጠቃላይ ሐብት ያለው ሲሆን ከአስር ሺህ በላይ ሰራተኞችንም ያስተዳድራል።