Search

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ አንዱ ማጠንጠኛ

ዓርብ ታኅሣሥ 17, 2018 642

ያዕቆብ /ማርያም (/) “አሰብ የማን ናት?” በሚለው መጽሐፋቸው፣ ኢትዮጵያ አሰብን ያጣችበትን ሁኔታና የባሕር በር የሌላት ሀገር መሆኗ የሚያስከትለውን ቀጣይ ጉዳት በታሪክና በሕግ ሰነዶች አስደግፈው አስረድተዋል።

በግንቦት 1983 . የተጠራው የሰላም ጉባኤ፣ የኤርትራን ነፃነት በማጽደቅ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል መወሰኑን ዶክተር ያዕቆብ በመፅሐፋቸው ገልጸዋል።

ይህ ጉባኤ በሕዝብ ያልተመረጡ ተወካዮች የተገኙበት በመሆኑ፣ ሀገር የማፍረስ ሕገ-ወጥ ውሳኔ ለማስተላለፍ ሥልጣን እንደሌለውም በስፋት አስቀምጠዋል።

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከጸደቀው 1923 . ሕገ-መንግሥት አንስቶ እስከ ደርግ መመሪያዎች ድረስ፣ የኢትዮጵያን አንድ ስንዝር መሬት ለሌላ አሳልፎ መስጠት ወይም ማንኛውንም የኢትዮጵያ ክፍል ማስገንጠል እንደማይፈቅድ መፅሐፉ ያብራራል።

እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ሊተላለፍ የሚችለው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) ሲስማማ ብቻ ቢሆንም፣ ሕዝብ ባልወሰነበት ሁኔታ 'አውድማህ ለሌላ ሰው ተላልፎ ተሰጥቷል' እንደተባለ ጭሰኛ አርሶ አደር፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቁጭቱን ይዞ ባሕር በሩን እያሰበ ቆይቷል።

ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ በአልጀርስ ሥምምነት ወቅት ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብ ባለቤትነት መብቷን አንስታ የምታስከብርበት መልካም አጋጣሚ እንደነበር ቢገልጹም፣ ኢህአዴግ በወቅቱ ታሪካዊና ሕጋዊ መብቷን ለማስከበር ጥረት አለማድረጉም በርካቶችን አስቆጭቷል።

ይህንን የታሪክና የሕግ ጥያቄ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) “የመደመር መንግሥትበተሰኘው መጽሐፋቸው፣ የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጽሐፋቸው፤ ኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥር እያደገች ያለች አገር እንደመሆኗ፣ የወደብ አልባነት ዕጣ ፈንታ ለኢኮኖሚ ዕድገቷና ለብሔራዊ ደኅንነቷ ትልቅ ማነቆ መሆኑን አሳይተዋል።

በተለይም በመደመር እሳቤ፣ የባሕር በር ጥያቄን ከቀጣናዊ ትስስርና ከጋራ ብልጽግና አንጻር ይመለከቱታል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘቷ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ሰላምና ለጎረቤት ሀገራትም የኢኮኖሚ መነቃቃት እንደሚፈጥር በመግለጽ፣ ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ (Win-Win approach) ሊፈታ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ካላት ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ አቅም አንጻር፣ የወደብ ጥያቄዋ ተገቢና ዓለም አቀፍ ሕጎችን የተከተለ መሆኑን ያመላክታል።

በአሁኑ ወቅት ይህ ቁጭት አዘል ጥያቄ ብሔራዊ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የትውልድ ቁጭት ሆኖ መቅረብ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ተቀባይነትም ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ይገኛል።

ኢትዮጵያም ይህንን ፍላጎት ለማሳካት በሰላማዊ መንገድ እና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገች ይገኛል።

የባሕር በር ጥያቄው መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ወዳጆች ከመሻት ባለፈ የተጠናከረ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው የፖለቲካ ተንታኞችም አፅንዖት ይሰጣሉ።

አንድ ሕዝብ በእውነተኛ እና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በአንድነት ዓላማውን ለማሳካት ከጣረ ከግብ የማይደርስበት ምክንያት አይኖረውም።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄም ዓለም የተስማማበት ፍትሐዊ ጥያቄ ሆኖ ሳለ ጉዳዩን ጊዜ እስኪፈታው ይቆይ ብሎ መጠበቅ ሳይሆን፣ ሁሉም ዜጋ በሚችለው ሁሉ ጥረት ሊያደርግበት የሚገባ ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑ ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም።