Search

ዴልታ ወርክስ በችግር ተፀንሶ በ43 ዓመታት ፅናት የተወለደው አስደናቂ የምኅንድስና ጥበብ

ማክሰኞ ታኅሣሥ 21, 2018 4852

በአውሮፓውያኑ ወርሃ ጥር 1953 ከሰሜን ባሕር ላይ የተነሳ ከፍተኛ ማዕበል ከባሕር ጠለል በታች የሚገኙትን የኔዘርላንድ ከተሞች በማጥለቅለቅ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ።
ይህ በኔዘርላንስ ታሪክ አስከፊ ጉዳት ያደረሰ ማዕበል በኔዘርላንድስ ደቡብ ምዕራብ ክፍል የሚገኙ በርካታ ከተሞችንና መንደሮችን አውድሟል።
በተለይ በዜይላንድ ደቡብ ሆላንድ እና ኖርዝ ብራባንት በተባሉ ግዛቶች የሚገኙ በርካታ መንደሮች በሀይለኛ ጎርፍ ተጥለቅልቀው ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባቸው።
በዚህ ያልታሰበ የተፈጥሮ አደጋ ምክንያትም በወቅቱ 1ሺህ 836 ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ 10 ሺህ በላይ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። ከዚህ በላይም 38 ሺህ ቤቶች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ 30 ሺህ በላይ እንስሳትም አልቀዋል።
ይህ በሀገሪቱ ታሪክ አስከፊ የሆነው አደጋ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ካለፈ በኋላ የኔዘርላንድስ መንግስት ዳግመኛ እንዲህ አይነት ሰቆቃ እንዳይከሰት የሚከላከል ታላቅ ግንብ ለመገንባት አቅዶ ወደተግባር ገባ።
አደጋው በደረሰ በ20 ቀናት ውስጥም ይህንን ፕሮጀክት ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የሚያጠና የዴልታ ኮሚሽን የሚባል የጥናት ቡድን ተቋቋመ።
በኮሚሽኑ ጥናት መሰረትም ባጠቃላይ 700 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የባሕር ዳርቻ ለመጠበቅ የሚያስችል 30 ኪ.ሜትር ርዝመት ያላቸው 13 የማዕበል መከላከያ በሮች እና ሀይለኛውን ማዕበል ማገድ የሚችሉ ግንቦችን ለመገንባት ተወስኖ የዴልታ ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ።
ከወራት በኋላም በ1954 ግንባታው በአንጻራዊ ሁኔታ ቀላል በሆኑና ጥልቅ ባልሆኑ የባሕሩ ዳርቻዎች ላይ በመጀመር ግንባታው ተጀመረ።
ይህ አይነት አውዳሚ የሆነ የጎርፍ አደጋ በረጅም ዓመታት አንዴ ሊከሰት የሚችል እንደሆነ ቢገመትም ባልታሰበ ጊዜ ተከስቶ ጉዳት እንዳያደርስ በሚል ጥንቃቄ ሰባት ቢሊየን ዶላር የሚፈጀውን ታላቅ ፕሮጀክት የመገንባቱ ስራ ቀጠለ።
 
በባሕር ወለል ላይ የሚተከሉት ምሶሶዎቹ እንዳይሰምጡ በሚሊየን ቶን የሚገመት የድንጋይና የአሸዋ ንጣፎች በባሕር ስር ተደለደሉ።
እነዚህን እያንዳንዳቸው ብዙ ሺህ ቶን የሚመዝኑ የኮንክሪት ምሰሶዎች ተሸክመው ባሕር ውስጥ መትከል የሚችሉ ትላልቅ የኮንስትራክሽን መርከቦች በልዩ ትእዛዝ ተሰርተው አገልግሎት ላይ ዋሉ።
ከቀላል ፕሮጀክቶች የተጀመረው መከለያ ግምብ ወደከባዱ እየሄደ የባሕሩን ውሃ የሚያስተነፍሱ እንደ Haringvliet ያሉ ትላልቅ ግድቦች በባሕሩና በመሬቱ መካከል ተገነቡ።
በዚህ መልኩ ከ1954 እስከ 1997 ዓ.ም ለዓመታት የተካሄደው የዴልታ ፕሮጀክት ስራው ሲጀመር ያልነበሩ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በቀድሞው ዲዛይን ላይ እያካተተ ሲገነባ ለ43 ዓመታት ዘልቋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ስድስት የተለያዩ መንግስታት ተቀያይረዋል።
 
ይሁን እንጂ ሁሉም መንግስታት ለፕሮጀክቱ ያላቸውን ቁርጠኝነትና በጀት ሳይቀንሱ ለተተኪው አስረክበዋል፡፡
በእነዚህ ረጅም የግንባታ ዓመታት ኔዘርላንድስ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ አልፋለች። በተለይ በ1970ዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ በብዙ ሀገራት የኢኮኖሚ ቀውስ አስከትሎ ያለፈው የነዳጅ ዘይት ዋጋ አለመረጋጋት የኔዘርላንድስንም ኢኮኖሚ በእጅጉ ጎድቶት የነበር ቢሆንም ይህ ብሄራዊ ፕሮጀክት ላፍታ እንዲቆም አልተደረገም ነበር።
በዚህ ሁኔታ ኔዘርላንድስን ካልታሰበ የማእበልና የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የተጀመረው ፕሮጀክት ከዓመት አመት እየሄደ በየጊዜው የሚመጡ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎች ዘመናዊ የግንባታ ሂደቶችን በማካተት ለረጅም ዓመታት ግንባታው ሲካሄድ ከቆየ በኋላ በመጨረሻም 13 ማስተንፈሻ ግድቦችንና ማእበሉን የሚከላከሉ ግንቦች አልቀው ግንባታው በተጀመረ ከ43 ዓመታት በኋላ ተጠናቀቀ።
ከዓመታት በኋላ ዛሬ ላይ በእነዚህ ግድቦች ላይ አውራ ጎዳናዎች ተሰርተውባቸዋል። መኪናዎች በባሕሩ አናት ላይ ባሉ ግድቦች ላይም ይጓዛሉ።
ይህ የዓመታት የፅናት ውጤት እና የትውልድ ቅብብሎሽ ምልክት የሆነውን ታላቅ ፕሮጀክት በቱሪስቶች ከሚጎበኙ መስህቦች መካከል አንዱ ሲሆን የአሜሪካ የሲቪል ኢንጂነሮች ማህበር (ASCE) ከዓመታት በፊት ባወጣው ዘገባ መሰረት በዓለማችን ከሚገኙ አስደናቂ የምህንድስና ፕሮጀክቶች መካከል የዴልታ ፕሮጀክትን ስምንተኛው አስደናቂ ግንባታ አድርጎ መዝግቦታል።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ