Search

ከ40 በላይ ቻይናውያን ስፔሻሊስት ሐኪሞች ነፃ የሕክምና አገልግሎት እየሰጡ ነው

ሓሙስ ነሐሴ 01, 2017 130

ከ40 በላይ ቻይናውያን በጎ ፍቃደኛ ስፔሻሊስት ሐኪሞች በኢትዮጵያ የአንጎል እና የልብ ቀዶ ጥገናን ጨምሮ የተለያዩ ሕክምናዎችን በነጻ በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የማስጀመሪያ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ እየተሰጠ ላለው ነፃ የሕክምና አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስትሯ መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ ይህ አገልግሎት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።
ነፃ ሕክምናው በሲልክ ሮድ ሆስፒታል የሚሰጥ ሲሆን ከሐምሌ 30 ጀምሮ ለ15 ቀናት የሚቆይ ነው።
ሕክምናው በጤና ሚኒስቴር ለተለዩ ወደ 100 የሚሆኑ ታካሚዎች ተደራሽ እንደሚሆንም ነው የተገለፀው።
ትናንት በተደረገ የበጎ ፍቃድ ሕክምና አገልግሎቱ የጭንቅላት እና የዓይን ቀዶ ሕክምናዎች በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቃቸው ተገልጿል፡፡
ሦስት ህፃናት ደግሞ ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ ወደ ቻይና ሄደው እንዲታከሙ መወሰኑ ተጠቁሟል።
ከዚህ በተጨማሪም የበጎ ፈቃድ የሕክምና ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣም 1.2 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ግምት ያላቸው አላቂ እና አላቂ ያልሆኑ የሕክም ቁሳቁስ በድጋፍ መልክ ይዞ መምጣቱውም ተገልጿል።
የኢትዮጵያን እና የቻይናን ሁለትዮሽ ግንኙነት ያጠናክራል በተባለው በዚህ የነፃ ሕክምና አገልግሎትም፣ ኢትዮጵያውያን እና ቻይናውያን የጤና ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
 
በሴራን ታደሰ