ዛሬ ማሌዥያ ስትጠቀስ በአዕምሯችን የሚመጣው ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች፣ ጉግል፣ ማይክሮ ሶፍት እና ኢንቴልን ጨምሮ የተለያዩ ግዙፍ የቴክኖሎጂ እና ኤሌክትሮኒክስ ማዕከላት የሚገኙባት የበለፀገች ሀገር መሆኗን ነው።
ሆኖም ይህች ሰላማዊ እና የበለፀገች ሀገር ከጥቂት ዐሥርት ዓመታት በፊት ተካሂዶ ታሪኳን ከቀየረው ብሔራዊ ምክክር በፊት አስከፊ የሚባሉ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ዕረፍት የነሧት ሀገር ነበረች።
ከነዚህ ማሌዥያን ሰላም ከነሧት ችግሮች አንዱ በሀገሪቱ ውስጥ የነበረው የእርስ በርስ ግጭት እና በዚያ ምክንያት የመጣው የፖለቲካ አለመረጋጋት ነበር።
ይህ በማሌይ ተወላጆች እና የቻይና ዝርያ ባላቸው ዜጎች መካከል የተቀሰቀሰው የብሔር ግጭት ሀገሪቱን ወደ ገደል አፋፍ አድርሷት ማብቂያዋ የደረሰ አስመስሎት ነበር።
በእነዚህ ችግሮች ምክንያት ነገሮች ተባብሰው፣ የሀገሪቱ ፓርላማ ተበትኖ፣ በወታደራዊ አገዛዝ ሥር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በነበረችበት ወቅት የልማት አባት በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት ቱን አብዱልራዛቅ ቢን ሁሴን ወደ ሥልጣን መጡ።
ቱን አብዱልራዛቅ ይህን ከባድ ኃላፊነት ተሸክመው የመሪነት ቦታውን ከያዙ በኋላ ወዲያውኑ የወታደራዊው አገዛዝ እንዲያበቃ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ ወስነው 65 አባላት ያሉት ብሔራዊ ምክር ቤት አቋቋሙ።
ይህ በቱን አብዱልራዛቅ ቢን ሁሴን የተቋቋመው ምክር ቤት ዋንኛ ተልዕኮው በብሔረሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በጥልቀት መመርመር እና ለዘላቂ ብሔራዊ አንድነት መፍትሔ መፈለግ፣ የሚል ሲሆን ከገዢው ፓርቲ (UMNO) እና ከተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተውጣጡ የፖለቲካ መሪዎች 13ቱን የማሌዥያ ግዛቶች የሚወክሉ የክልል ተወካዮች የእስልምና፣ የቡድሂስት፣ የክርስትና እና የሂንዱ እምነት ተወካዮች የእንዲሁም የሙያ እና የሲቪክ ማኅበራትን ያካተተ ነበር።
ከዛም በዚህ መልኩ የተዋቀረው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያካተተ የምክክር ኮሚቴ ለሚዲያ ዝግ በሆነ ሁኔታ መምከር ጀመረ።
ሁሉም የውይይቱ ተሳታፊዎች የወከሉትን ሕዝብ ቅሬታ፣ ብሶት እና ችግራቸውን በይፋ በማቅረብ በመፍትሔው ላይ እየመከሩ ለስምንት ወራት ያህል በዝግ ከተወያዩ በኋላ እ.አ.አ ነሐሴ 31 ቀን 1970 ማሌዥያን እንደ አዲስ የሠራት፣ የብልፅግናዋ እና የሰላሟ መሠረት የሆነው ‘ሩኩን ነጋራ’ (Rukun Negara) የሚባለው የጋራ የስምምነት ሰነድ ተወለደ።
ይህ ማሌዥያውያን ለጋራ ሰላም እና ዕድገታቸው ለወራት ከተወያዩ በኋላ የፀደቀው ሰነድ በሕዝብ ዘንድ እንዲደርስ እና ተቀባይነት እንዲያገኝ ሰፊ ሥራ ይፈልግ ነበር።
በመጨረሻ ግን ማሌዥያን ከከፋ የመበታተን አደጋ አውጥተው ዛሬ ወደምትታወቅበት የብልፅግና ጎዳና እንድታመራ መሠረት የጣሉት ቱን አብዱልራዛቅ፣ የሀገሪቱ ብሔራዊ ፍልስፍና ሰነድ የሆነውን ‘ሩኩን ነጋራ’ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ ማሌዥያውያን የሰላም ሰነዳቸውን በሙሉ ልብ ተቀብለው ለተግባራዊነቱ በኅብረት መሥራት ጀመሩ።
የወራት ምክክር ውጤት የሆነው ‘ሩኩን ነጋራ’ የማሌዥያውያንን ሥነ-ልቡና ቀየረው። “ከብሔሬ በፊት ሀገሬ" የሚል መንፈስ በትምህርት ቤቶች፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና በዜጎች ልብ ውስጥ ሰረፀ።
ይህ ማሌዥያውያን በኅብረት ሆነው መክረው ያዘጋጁት ሰነድ በውስጡ ለፈጣሪ ስለ መገዛት፣ ለሀገረ መንግሥቱ ታማኝ ስለመሆን እንዲሁም ስለ አንድነት እና ኅብረት የሚሰብክ ነበር።
ማሌዥያ የብዙ እምነቶች ሀገር ብትሆንም ሁሉም ዜጋ በሃይማኖታዊ እሴቶች እንዲመራ እና ለፈጣሪ እንዲገዛ ያሳስባል። ይህ መርሕ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሞራል እና የሥነ-ምግባር መሠረት ለመጣል ታስቦ የተነደፈ ነው።
የሕግ የበላይነትን በተመለከተ ማንም ሰው ከሕግ በላይ አለመሆኑን እና ፍትሕ ያለ አድልዎ መከናወን እንዳለበት ያስተምራል። ዜጎች ለሀገራቸው ሉዓላዊነት እና ለሀገረ መንግሥቱ ሥርዓት ታማኝ እንዲሆኑ ይጠይቃል።
መልካም ሥነ-ምግባር እና ጨዋነትን በተመለከተም፣ ዜጎች እርስ በርሳቸው በመከባበር እንዲኖሩ ያሳስባል። በተለይም በተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል ግጭት እንዳይነሣ ባህልን እና ስሜትን ማክበር ወሳኝ መሆኑን አፅንኦት ይሰጣል።
የሕገ-መንግሥትን የበላይነት በተመለከተም ሕገ-መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ መሆኑን ማክበር እንደ አንዱ ምሰሶ ያስቀምጣል፤ ይህ መርሕ የዜጎችን መብት እና ግዴታ የሚያስከብር በመሆኑም ማንኛውም የመንግሥትም ሆነ የግል እርምጃ ከሕገ-መንግሥቱ መውጣት እንደሌለበት ያስገነዝባል።
በዚህ መልኩ የማሌዥያ ሕዝብ በብሔራዊ ደረጃ ተሰባስቦ መክሮ ያፀደቀው የጋራ ሰነድ ተማሪዎች በየትምህርት ቤቱ የሚማሩት፣ በየመሥሪያ ቤቱ የሚተገበር፣ በፋብሪካ እና ኢንደስትሪዎች በሥራ ላይ የሚውል፣ ማሌዥያውያን ወድደው እና ፈቅደው ከልብ የተቀበሉት ሕግ መሆን ቻለ።
ከዚህ በኋላም፣ አርቆ አሳቢው መሪ ቱን አብዱልራዛቅ በብሔራዊ ምክክር የመጣውን ሰላም እና በ‘ሩኩን ነጋራ’ መፅናት የጀመረችውን ማሌዥያን ለማሳደግ እና ኢኮኖሚዋን ለመለወጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መሥራት ጀመሩ።
ይህም ተሳክቶ ማሌዥያን በብልፅግና ጎዳና ለመምራት የሚያስችል የ50 ዓመታት የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ነድፈው ለተግባራዊነቱም መንቀሳቀስ እና መሠረት መጣል ጀመሩ።
ከዓመታት በፊት በዚህ መልኩ የተጀመረው የኢኮኖሚ ስትራቴጂ መሠረትም ማሌዥያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ተጉዛ ኢኮኖሚዋን ከመቀየርም ባለፈ፣ የዓለማችን ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ተርታ ስሟን ማስጠራትና የሕዝቧን ህይወት በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻል የቻለች ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ ከአለም ጋር ለመሽቀዳደም ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚወስዳትን ጉዞ ጀምራለች።
በዋሲሁን ተስፋዬ
#EBC #ebcdotstream #Nationaldialogue #Malaysia #RukunNegara