“የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ስፔክትረም ልዕልና ለሀገር ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሐሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነ የኤሌክትሮኒክ ዋርፌር አውደ ጥናት በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና መሥሪያ ቤት ዛሬ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ኤሌክትሮኒክ ዋርፌር አማራጭ ቅንጦት (Luxury) አይደለም፤ ይልቁንም የ21ኛው ክፍለ ዘመን ለሀገራት ሉዓላዊነት መሠረት ነው ብለዋል፡፡
ዛሬ የምንገኝበት ዘመን የጦርነት፣ የፉክክርና የሀገራት ኃይል መገለጫዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀያየሩ ያሉበት ወቅት ነው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፤ ከዚህ ቀደም ሀገራት ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት ሩጫ በመሬት፣ በባሕር፣ በአየርና በሕዋ ክልል በሚደረጉ ፍልሚያዎች ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ዛሬ ግን ዘመናዊው ውጊያ እነዚህን ድንበሮች አልፎ በማይታይ፣ ነገር ግን የጦርነቱን ዕጣ ፈንታ በሚወስን ረቂቅ የኤሌክትሮማግኔቲክ ስፔክትረም ምሕዳር ውስጥ ሆኗል ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ለኢትዮጵያ የኤሌክትሮማግኔቲክ ስፔክትረምን መጠቀም የደህንነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሰፊ የቆዳ ስፋትና ተለዋዋጭ የሆነው ቀጣናዊ ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ ካለን ተጨባጭ የመከላከል አቅም ጋር መመጣጠን ይኖርበታል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው፤ የዘመኑ ጂኦፖለቲካዊ ፉክክር መልክ እየቀየረ መጥቶ፣ የሀገር ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው በመሬት፣ በባሕር፣ በአየር፣ በሕዋ፣ ወይም በሳይበር ላይ በሚደረግ ተጋድሎ ብቻ ሳይሆን፤ በማይዳሰሰውና ረቂቅ በሆነው የኤሌክትሮማግኔቲክ ስፔክትረም እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

አውደ ጥናቱ የተዘጋጀውም ይህንን የፉክክር ዘርፍ በብቃት ለመረዳትና በስፔክትረሙ ላይ አስተማማኝ የበላይነትን ለመጨበጥ የሚያስችለንን ብሔራዊ አቅም ለመገንባት ነው ብለዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም፤ የኢትዮጵያን ሰላምና ህልውና የሚያስጠብቁ ቁልፍ ተቋማት መሪዎች በአንድነት መሰባሰባቸው፤ ኢትዮጵያ ለሚገጥሟት ዘመናዊ የጸጥታ ስጋቶች የምትሰጠው ምላሽ በሳይንሳዊ ትንታኔ እና በተቋማዊ ቅንጅት ላይ የተመሠረተ መሆኑን የሚያበስርና ይህን ግብ ለማሳካት ያለንን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በየተቋማቱ የሚገኙ እምቅ አቅሞችን መደመርና ተቋማዊ ቅንጅትን (Institutional Synergy) መፍጠርም የመድረኩ ትኩረት መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሀገራት ደህንነት የሚረጋገጠው ባሰለፉት የሰው ኃይል ቁጥር ወይም በታንኮች ብዛት ብቻ አይደለም ያሉት ደግሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ናቸው፡፡
ይልቁንም መረጃን ቀድሞ የማግኘት፣ ስፔክትረሙን የመቆጣጠርና ጠላት እንዳይጠቀምበት የማድረግ የቴክኖሎጂ የበላይነት ጭምር መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም ይህንን ምሕዳር የተቆጣጠረ ወገን መረጃን ቀድሞ የማግኘት፣ ውሳኔን በፍጥነት የመወሰንና የድል ልዕልናን የመያዝ ስትራቴጂካዊ ብልጫ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የኤሌክትሮኒክ ዋርፌር ታሪካዊ ዳራ፣ አሁናዊ የሀገራት ተሞክሮ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ወቅታዊና መጻኢ ሁኔታዎችን የዳሰሰ መነሻ ጽሑፍ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ ቀርቧል፡፡ በገለጻውም የኢትዮጵያ የኤሌክትሮማግኔቲክ ስፔክትረም ልዕልና ለማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ በዝርዝር ቀርቧል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ የተለያዩ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተካፈሉበት የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የኢፌዲሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌ/ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፣ በመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ የኤሌክትሮኒክ ዋርፌር መምሪያ ኃላፊ ኮ/ል አሸናፊ ኦሊ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኃይለማርያም በፓናሊስትነት ተሳትፈዋል፡፡ ውይይቱን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ም/ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ሲሳይ ቶላ መርተውታል፡፡
የፓናል ውይይቱ በዋናነት የኤሌክትሮማግኔቲክ ስፔክትረምን በአግባቡ በመቆጣጠርና በመምራት የኢትዮጵያን አሁናዊና መጻኢ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ዘርፉን የሚመሩ ተቋማት መገንባት፣ በዘርፉ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮችን ማላቅ፣ እንዲሁም በባለድርሻ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብርና ቅንጅት ይበልጥ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡