የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መሪ አቶ እዮብ መሳፍንት ከኢቲቪ ወቅታዊ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የድህረ ምርጫ ወቅታዊ ሁኔታዎችንና የፓርቲያቸውን የቀጣይ የፖለቲካ አቅጣጫ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
መሪው በምርጫው ወቅት የታየውን ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ያደነቁ ሲሆን፣ ሕዝቡ በተለያዩ ተግዳሮቶች ሳይበግረው ረጅም ሰዓት ተሰልፎ መምረጡ ከሰላማዊ አማራጭ ውጪ በጠመንጃ ሥልጣን የመያዝ አባዜ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ሙሉ በሙሉ መወገድ እንዳለበት ያሳየበት ግልጽ መልዕክት ነው ብለዋል፡፡
ኢዜማ ወደ ምርጫው የገባው የኢትዮጵያን ተጨባጭ የፖለቲካ ምኅዳር በጥልቀት ገምግሞ መሆኑን የገለጹት አቶ እዮብ፣ ፓርቲው አስቀድሞ ካስቀመጠው ግብ አንጻር የአሁኑ ተሳትፎው ከሞላ ጎደል ስኬታማ እንደነበርና ምርጫ ሲደርስ ብቻ የሚደናገጥ ሳይሆን ራሱን ወዲያውኑ ለቀጣዩ ምርጫ ማዘጋጀት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
ኢዜማ በክልልና በፌደራል ምክር ቤቶች በድምሩ 86 ወንበሮች ማግኘቱን የጠቀሱት መሪው፣ እነዚህን ወንበሮች በመጠቀም አማራጭ ፖሊሲዎችን ወደፊት ለመግፋትና መንግሥትን ለመጠየቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩበት አረጋግጠዋል፡፡
አያይዘውም አሁን ለተመረጠው መንግሥት የተሰጠው ኃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር የተሰጠ ሕዝባዊ አደራ እንጂ እንደፈለጉ የሚፈነጩበት ሥልጣን አለመሆኑን አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የምርጫ ሥርዓት ተቀይሮ የአንድም ዜጋ ድምፅ እንዳይባክን የሚያደርግ “የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት” ሊተገበር እንደሚገባ ፓርቲያቸው በፅኑ እንደሚያምንና ኢትዮጵያ ውስጥ ከፖለቲካና ከዘውግ ወገንተኝነት የጸዱ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረቱ ገለልተኛ ተቋማትን (Institutions) ለመገንባት የገዥው ፓርቲ ቀዳሚ ኃላፊነት ቢሆንም የሁላችንም የጋራ ርብርብ ያስፈልገናል ብለዋል፡፡
የባሕር በር ጉዳይን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት አቶ እዮብ መሳፍንት፣ የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት ሀገር የልማት፣ የዕድገትና የደኅንነት ዋስትና መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን ብሔራዊ ጥቅም ከፊት ሆኖ ከሚያራምድ ከማንኛውም አካልና ከመንግሥት ጋር በትብብር ለመሥራት ፓርቲያቸው ዝግጁ መሆኑን በድፍረት ተናግረዋል፡፡
በመሐመድ ፊጣሞ