Search

ልዩነቶችን በምክክር አደባባይ መፍታት፤ የጠብመንጃ ፖለቲካን አክስሞ የነገዋን ጠንካራ ኢትዮጵያ ለመገንባት የተያዘው ታሪካዊና ስኬታማ ጉዞ

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 55

ኢትዮጵያ ካጋጠሟት ታሪካዊና መዋቅራዊ ችግሮች ወጥታ አስተማማኝ የሀገረ መንግሥት መሠረት መጣል የምትችለው ዜጎቿ ልዩነቶቻቸውን በኃይል ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ማስተናገድ ሲችሉ ብቻ እንደሆነ በተግባር እየታየ ነው፡፡

ላለፉት ዓመታት  ሲካሄድ የነበረው ሰፊ ሕዝባዊ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፥ ከአርሶ አደር እስከ ምሁር፣ ከሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እስከ ወጣቶችና ሴቶች ድረስ እያንዳንዱን የማኅበረሰብ ክፍል ያካተተ ነበር፡፡

ይህ እስካሁን የተጓዝንበት ስኬታማና አካታች መንገድ፥ በሀገራችን ውስጥ የቆዩ መዋቅራዊ ቅራኔዎችን በዘላቂነት ለመፍታትና የጠብመንጃ ፖለቲካን ጨርሶ ለማክሰም የሚያስችል የማይናወጥ ሕዝባዊ መሠረት ጥሏል፡፡

ይህ በልዩነት ውስጥ መደማመጥንና በውይይት መፍትሔ መፈለግን ያማከለው ታሪካዊ ሂደት፥ ዛሬ ላይ ትልቅ እምነትና መነቃቃትን ፈጥሮ ወደ ቀጣዩና ወሳኙ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡

ኮሚሽኑ በሰፊው ሕዝባዊ ተሳትፎ ያሰባሰባቸውን ስምንት አንኳር አጀንዳዎች ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ አሁን መላው ህዝብ ፊቱን ወደ ታላቁ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ አዙሯል፡፡

ይህም ማለት ትናንት በተበታተነና በየአካባቢው በተደረጉ ውይይቶች የተነሱ የዜጎች ሕመሞች፣ ሥጋቶችና የነገ ምኞቶች ሁሉ ተለቅመው፥ ነገ በጋራ መድረክ ላይ በጥንቃቄ ተመክሮባቸው ለዘላቂ ሰላም፣ ፍትሕና ብልጽግና የሚበጁ የጋራ ምክረ-ሃሳቦችና መፍትሔዎች የሚቀረጹበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ሊጀመር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚሠራቸው እነዚህ ሥራዎች ዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገዋን ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችሉ መሆናቸውን ዜጎች ተገንዝበዋል፡፡

በአሸናፊና ተሸናፊ ሥነ-ልቦና ሳይሆን ሁሉም ወገን በእኩልነት አሸናፊ የሚሆንበትን ይህንን ሥልጡን የሰላም መንገድ በቅንነት መደገፍና በንቃት መከታተል የእያንዳንዱ ዜጋ የሕልውና እና የሰላም አደራ ነው፡፡

በብሌን ደምበሎ