በ23ኛው የዓለም ዋንጫ የምድብ ዘጠኝ ተጠባቂ የመጨረሻ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ዛሬ ምሽት 4:00 ሰዓት ላይ ሲደረጉ፣ የምድቡን መሪ ለመለየትና የምርጥ ሦስተኛ ደረጃ ዕድልን ለመጠቀም ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የዓለም ዋንጫን ሁለት ጊዜ ማንሳት የቻለችው ፈረንሳይ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ኖርዌይን ትገጥማለች፡፡
ፈረንሳይ ካደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች ሁለቱንም በማሸነፍ፣ 6 ግቦችን አስቆጥራ 1 ብቻ በማስተናገድ በ6 ነጥብ የምድቡ መሪ ነች።
በአንጻሩ ኖርዌይ ካደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች ሁለቱንም በማሸነፍ፣ 6 ነጥብ ይዛ በግብ ክፍያ በፈረንሳይ ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ኖርዌይ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኳ በ1998 እስከ ጥሎ ማለፍ ድረስ መጓዝ የቻለችበት ታሪክ ያላት ሲሆን፣ ዛሬ ከፈረንሳይ ጋር በምታደርገው ጨዋታ የምድቡን የበላይነት ለመያዝ ትጫወታለች።
ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች ቀደም ብለው ባከናወኗቸው የምድብ ጨዋታዎች ላይ ባስመዘገቡት ድል ወደ ቀጣይ ዙር ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፣ የዛሬውን ጨዋታ ምድቡን በአንደኝነት ለማጠናቀቅ ይጫወታሉ፡፡
በሌላኛው መርኃ ግብር ሴኔጋል ከኢራቅ ጋር በምታደርገው ጨዋታ ምርጥ ሦስተኛ ሆና ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ያላት ዕድል ጠባብ ሲሆን፣ ምንም እንኳ በእርሷ ማሸነፍ ብቻ የሚወሰን ባይሆንም ብሎም በምታስመዘግባቸው ግቦች ብዛት ቢመረኮዝም፣ በዚያ ጠባብ ዕድል ለመጠቀም የሚደረግ ወሳኝ ፍልሚያ ነው።
ሴኔጋል ካደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች በሁለቱም በመሸነፏ ካለምንም ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በ2002 የኮሪያ እና ጃፓን ዓለም ዋንጫ እስከ ሩብ ፍፃሜ ተጉዛ ታሪክ የጻፈችው ሴኔጋል፣ ዛሬ ኢራቅን በማሸነፍ ምርጥ ሦስተኛ ሆና ለማለፍ ያላትን ጠባብ ዕድል ለመጠቀም ትጫወታለች።
ኢራቅ በበኩሏ ካደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች በሁለቱም በመሸነፏ፣ ከምድቡ የተሰናበተች ለመርኃ ግብር ማሟያ እና ለታሪክ ጨዋታዋን ታከናውናለች።
በአሁኑ ሰዓት ስዊድን እና ኢኳዶር በ4 ነጥብ ምርጥ ሦስተኛ ሆነው ለማለፍ ያለውን ዝርዝር እየመሩ ሲሆን፣ የዚህ ምድብ ውጤትም በምርጥ ሦስተኛነት በሚያልፉ ሀገራት ዝርዝር ላይ የራሱ ተጽዕኖ ይኖረዋል።
በዘረንቶስ ሰለሞን