Search

ከችግኝ ተከላ እስከ ጣፋጩ ማር፤ የአረንጓዴ ዐሻራ በኢትዮጵያ ማር ምርት ላይ ያመጣው ተጨባጭ ለውጥ

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 51

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከአየር ንብረት ጥበቃና የደን ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ ለተፈጥሮ ሚዛን መስተካከልና ለብዝኃ-ሕይወት መበልጸግ የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተቀናጀ የችግኝ ተከላና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የሀገራችንን የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።

ይህም ለንብ ዝርያዎች መራባትና ኅልውና ወሳኝ የሆኑ አበቦች፣ ዕፅዋትና ተፈጥሯዊ መጠለያዎችን መልሶ በመተካት ረገድ ምቹና ተስማሚ የሥነ-ምህዳር ከባቢን መፍጠር አስችሏል።

ንብ እርባታ በቀጥታ ከዕፅዋትና ከአበቦች መኖር ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣  በመርሐ ግብሩ አማካኝነት የሚተከሉ ችግኞች ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን፣ ለምግብ ዋስትና እና ለንብ ማር ምርት ምቹ ሁኔታን መፍጠር ችሏል።

በዚህም ምክንያት ንቦች በሰፊው የሚሰማሩባቸውን የላቀ የአበባ መስኮች በመፈጠራቸው በቂና ጥራት ያለውን የምግብ ምንጭ በማግኘት በሀገራችን  የሚመረተው የማር መጠንና ጥራት በተጨባጭ እንዲያድግ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል።

ይህ የማር ምርት ዕድገት በአየር ንብረት ጥበቃና በምግብ ዋስትና መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ለሚገኙ አርሶ አደሮችና ማኅበረሰቦች አዲስ የገቢ ምንጭ የፈጠረ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ማሳያ ነው።

ከተፈጥሮ ጥበቃ ጎን ለጎን የሚገኘው ይህ ዕድል፣ አርሶ አደሩ የአካባቢውን ደን እንዲጠብቅና ከግብርናው ዘርፍ የሚያገኘውን ገቢ በንብ እርባታ እንዲያባዛ የጎላ ፋይዳ አበርክቷል።

መርሐ ግብሩ  ተስፋን መትከል ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር ሊለወጥ የሚችልና ዘላቂነት ያለውን ኢኮኖሚያዊ አቅም በሀገር በቀል እውቀትና በተፈጥሮ ጸጋ ላይ እየገነባ መሆኑን ያረጋግጣል።

ይህ ዓይነቱ የተቀናጀ ልማትም ተፈጥሮን የመንከባከብ ተግባር እንዴት በቀጥታ ወደ ማኅበረሰባዊ ብልጽግና እና ወደ ሀገራዊ የምግብ ዋስትና ሊሸጋገር እንደሚችል በተግባር ያሳየ ጥልቅ ስትራቴጂ ነው።

በሔዋን ጌታቸው