ከቤት የሚጀምረው ጥልቅ እንክብካቤና የእናትነት ታላቅ ኃላፊነት ወደ ዱር ዘልቆ በመግባት፣ ተፈጥሮንና የዱር እንስሳትን በፅናት በመጠበቅ ረገድ በዓለም ዙሪያ የማይተካ ሚና እያበረከቱ ያሉ ጀግና ሴቶች መገኛ ሆኗል።
በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አማካኝነት ከሰኔ 23 እስከ ሰኔ 30 ድረስ የሚከበረው "ዓለም አቀፍ ሴት የዱር እንስሳት ጠባቂዎች/ሬንጀሮች ሳምንት" (World Female Ranger Week) እነዚህን ደፋር እንስቶች በደመቀ ሁኔታ ለማክበርና ለማበረታታት የሚውል ታላቅ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ነው።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ የተሰማሩ ሴቶች ቁጥር ከ11 በመቶ በታች ቢሆንም፣ በተፈጥሮ ጥበቃ፣ በማኅበረሰብ ተሳትፎ እና በሕገ-ወጥ አደን መከላከል ላይ የሚያሳርፉት ተጽዕኖ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የዘንድሮው የሳምንቱ መሪ ቃል "ተጽዕኖ" በሚል መመረጡ ተገቢነቱን ያሳያል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ሴቶች በዚህ አስቸጋሪ ተግባር ላይ ከፍተኛ የጀግንነት አሻራ እያበረከቱ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ የምትሰራውን ፈቲያ ኡስማንን ስናነሳ በከፍተኛ ኩራት ነው።
ፈቲያ ከ50 ሀገራት የተውጣጡ 140 ተወዳዳሪዎች በተሳተፉበት የዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ጥበቃ ህብረት (IUCN) የሬንጀሮች ውድድር ላይ ከአፍሪካ ለመሸለም ከበቁት ሁለት ሴት ሬንጀሮች መካከል አንዷ ሆና በመመረጥ ታላቅ ድል አምጥታለች።
ሌላኛዋ የለውጥ ተምሳሌት መኪቱ ደግሞ በአቢጃታ–ሻላ ብሔራዊ ፓርክ በሚገኙ ሐይቆች ጥበቃ ላይ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በንቃት በማሳተፍ የሬንጀር አስተባባሪ በመሆን ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከተች ድንቅ ሴት ናት።
በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ስሟ የጎላው ሬታ ፍራንቼስካ ዮሪ የተሰኘችው የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ፣ በአፍሪካ ቀንድ በሰውና በዱር እንስሳት መካከል የሚፈጠረውን ግጭት እንዲሁም ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ንግድን ለመከላከል በስትራቴጂ፣ በፖሊሲና በጥናት ዘርፍ በከፍተኛ እውቅና የሰራች የሀገራችን የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለውለታ ናት።
ይህ የሴቶች የጀግንነት ታሪክ በዓለም አቀፍ ደረጃም ደምቆ የሚታይ ሲሆን፣ ከደቡብ አፍሪካ የሚነሳው "ብላክ ማምባ" ሙሉ በሙሉ ሴቶችን ብቻ ያቀፈና ሳይታጠቁ በልዩ የጥበቃ ስልት የሚንቀሳቀስ የዓለማችን የመጀመሪያው የጸረ-አደን ቡድን ነው።
ይህ ቡድን በክሩገር ብሔራዊ ፓርክ የሽቦ ወጥመዶችን በተሳካ ሁኔታ በማስወገድና ሕገ-ወጥ አደንን በመከላከል ስሙ ናኝቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ "የጊር ንግስቶች" በመባል የሚታወቁት የህንድ የጊር ደን ሴት ሬንጀሮች፣ በዓለም ላይ በዱር ተፈጥሮ ውስጥ የቀሩትን ብቸኛ የእስያ አንበሶች በትጋትና በጥበብ በመጠበቅ ትልቅ አሻራ አሳርፈዋል።
በአጠቃላይ እነዚህ የተጠቀሱትን እንጂ በኢትዮጵያ በርካታ እንስቶች ተፈጥሮን ከመጠበቅ ባለፈ፣ የአካባቢያቸውን ማኅበራዊ አመለካከት በመቀየር፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለማኅበረሰባቸው አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን በመፍጠር የለውጥ ፋና ወጊ ሆነዋል።
በመሆኑም ለተፈጥሮ ህልውና እና ለዱር እንስሳት ጥበቃ በተግባር የተፈተኑና ዘላቂ ተጽዕኖ ላመጡ ለእነዚህ ጀግና ሴት ሬንጀሮች ተገቢውን ክብር ለመስጠት ይህ ሳምንት በዓለም ዙሪያ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።
በልዩ እሸቱ