Search

51ኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች

ማክሰኞ ታኅሣሥ 28, 2018 328

1. የማዳበሪያ ምርት ፈቃድ እና የፖታሽ ማዕድን ምርት ፈቃድ ረቂቅ ስምምነቶችን በተመለከተ
• ሁለቱ ረቂቅ ስምምነቶች የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ሀገራችን ለማዳበሪያ ግዥ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ለማስቀረት እና ለሀገራችን አርሶ አደሮች ወቅቱን የጠበቀ የማዳበሪያ ሥርጭት እንዲኖር ለማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው።
• ከአካባቢ ጥበቃ እና ከማኅበረሰብ ተጠቃሚነት አንጻርም የመንግሥትን የፖሊሲ አቅጣጫ የተከተሉ መሆናቸውን በማረጋገጥ የማዕድን ሚኒስቴር ስምምነቶቹን እንዲፈራረም እና ወደ ሥራ እንዲገቡ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ ይሁንታ ሰጥቷል።
2. የቤት ልማት ረቂቅ ፖሊሲ
• ባለፉት ዓመታት በቂ የቤት አቅርቦት እንዲኖር የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም አሁንም የቤት አቅርቦት እና ፍላጎት የተጣጣመ አይደለም።
• በመሆኑም በከተማና በገጠር ለሚኖሩ ለሁሉም ዜጎች አቅምን ያገናዘበ፣ ተደራሽ እና በቂ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፍ መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ቀርቧል።
• ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።
3. ከኮሪያ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ ጋር የተደረገው የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት
• የብድር ስምምነቱ ለሕከምና መሣሪያዎች አቅርቦት ፕሮጀክት ምዕራፍ 2 ማስፈፀሚያ የሚውል 30 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያስገኝ ነው።
• የሕክምና መሣሪያዎችን ችግር የሚፈታ፣ ዝቅተኛ ወለድ 0.01% የሚከፈልበት እና የ5 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው።
• ምክር ቤቱም ብድሩ ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም መሆኑን በማረጋገጥ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡
4. የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ለሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች የሚከፈል የአገልግሎት ክፍያን ለመወሰን የወጣ ደንብ
• ረቂቅ ደንቡ የተዘጋጀው ተቋሙ ለተገልጋዮች ጥራት እና ተዓማኒነት ያላቸው አገልግሎቶች ለመስጠት የሚያወጣቸውን ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ወጪዎች የአገልግሎቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ከሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ተመጣጣኝ ከፍያ በማስከፈል እንዲሸፍን ለማድረግ ነው።
• ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።
5. የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማሻሻያ አዋጅ
• በሥራ ላይ ያለው የኅብረት ሥራ ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 985/2009 ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከተቀመጡ አቅጣጫዎች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ አዋጁን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማሻሻያ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል።
• ምክር ቤቱም በማሻሻያ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።
6. የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ሴኩዩሪቲ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ
• ማሻሻያ አዋጁ የተዘጋጀው በአየር ትራንስፖርት ደኅንነት፣ አስተማማኝነት እና ቅልጥፍና ላይ የሚስተዋሉ የደኅንነት ስጋቶችን በብቃት ለመከላከል የሚያስችል አሠራር ለመተግበር የአቪዬሽን ሴኩዩሪቲ አዋጅ ቁጥር 432/1997ን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው።
• ምክር ቤቱም በማሻሻያ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።
7. ሁለቱ ደንቦች
7.1. የመሶብ አገልግሎትን ለማቋቋም የመጣው ደንብ
• ደንቡ ተገልጋዮች የመንግሥት አገልግሎት ለማግኘት የሚያባከኑትን ጊዜ፣ ወጭ እና ጉልበት በመቆጠብ የተገልጋይ እርካታን የሚጨምር የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ለመተግበር እንዲያስችል የቀረበ ነው።
7.2 የኢትዮጵያ የብቃት እና ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት አደረጃጀት፡ ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን የወጣው ደንብ
• ደንቡ ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር እና ኃላፊነት ለመወጣት እንዲያስችለው ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው።
• ምክር ቤቱም ሁለቱ ደንቦች በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረጉ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።
8. የሁሉን አቀፍ የተደራሽነት ፈንድ የገቢ መጠን፡ ምንጭ እና አስተዳደርን ለመወሰን የወጣ ደንብ
• ደንቡ በኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 1148/2011 አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ (3) መሠረት የተቋቋመው የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሁሉን አቀፍ ተደራሽነት ፈንድ የገቢ መጠን እና ምንጭ እንዲሁም ፈንዱ ስለሚተዳደርበት ሁኔታ ለመወሰን ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው።
• ምክር ቤቱም ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።
9. የኢፌዴሪ ስፖርት ፖሊሲን ማሻሻል
• በሥራ ላይ ያለው የስፖርት ፖሊሲ የማኅበረሰቡን የስፖርት ተሳትፎ ከማረጋገጥ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ሥርዓት ከመዘርጋት፣ ንፁህ ስፖርትን ለማስፋፋት የአበረታች ቅመሞች እና ዘዴዎች ከመከላከል እና ስፖርትን ለማኅበራዊ ልማት ከመጠቀም አንጻር ክፍተቶች የነበሩበት በመሆኑ ፖሊሲውን ለማሻሻል ረቂቁ ተዘጋጅቷል።
• ምክር ቤቱም ፖሊሲው ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ ወስኗል።
10. የፌዴራል ስፖርት ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ
• ረቂቅ አዋጁ የስፖርት ዘርፍ ካለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዲሁም አስተዳደራዊ ውስብስብነት አንፃር ዘርፉን በአግባቡ ለመምራት ዘመናዊ፣ አሳታፊ እና አካታች የሆነ የሕግ ማዕቀፍ እና አስተዳደራዊ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት የሚያስችል ነው።
• ምክር ቤቱም ረቂቅ አዋጁ ላይ ግብአቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።