ተቋማት የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችል አደረጃጀትና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖራቸው በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ አስታወቁ።
በመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም በመጀመሪያ ዙር የሚገቡ ተቋማት የዝግጅት ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
በአማራ ክልል እየተተገበረ የሚገኘው የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ሪፎርም የአመራሩንና የሠራተኛውን አቅም በከፍተኛ ደረጃ በማጎልበት፣ ለዜጎች የዘመነና ፈጣን አገልግሎትን በተደራሽነት ለመስጠት አልሞ በቁርጠኝነት እየተሰራበት ይገኛል።
የሪፎርሙ አፈጻጸም ዝግጅትና ትግበራ በጥልቀት በተገመገመበት በዚህ መድረክ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የክልሉ የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ባንችአምላክ ገብረማሪያምን ጨምሮ በሪፎርም ትግበራው ቀዳሚ የሆኑት የስምንት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩም የሪፎርሙ ዋና አምዶች የሆኑትን የአደረጃጀት ማሻሻያ፣ ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ ዲጂታል ሰርቪስ፣ ብዝሃና አካታች አገልግሎት እንዲሁም ምዘና እና ተጠያቂነትን በተግባር ለመተርጎም የተሠሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በተመለከተ ተቋማቱ ያሉበት ደረጃ ተገምግሞ ሰፊ ምክክር ተደርጎበታል።
በመድረኩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ ከተቋማት የዜጎችን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ የሚያስችል ቁመናና አገልግሎት አሰጣጥ እንደሚጠበቅ በጥብቅ አሳስበዋል።
የተገልጋይን እርካታ በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ የሪፎርሙ ቀዳሚና ዋነኛ ግብ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ይህ የተገልጋይ እርካታ ተሞክሮ በ"ሞሰብ አንድ ማዕከል" በተታየው ውጤታማ ትግበራና ፈጣን ምላሽ ልክ በተቋማቱ በሙሉ መሠራት እንደሚጠበቅበት ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ይህ ዓይነቱ የተቀናጀ የሪፎርም ንቅናቄም የቢሮክራሲ ማነቆዎችን በዘላቂነት በመቅረፍ፣ የሕዝቡን የዘመናት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በተጨባጭ ለመመለስ ታላቅ ተስፋ የተጣለበት ስትራቴጂካዊ እርምጃ መሆኑ በስፋት ተመላክቷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የሪፎርሙ ስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አህመዲን መሃመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሪፎርሙ የተቀናጀ መዋቅር፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርና ቁርጠኛ አመራርን የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀዋል።
ተቋማት ተስፋ ሠጪ የሪፎርም ትግበራ ላይ መሆናቸውን ተገንዝበናል ያሉት አህመዲን መሃመድ (ዶ/ር)፤ መድረኩ ሪፎርሙን የተቀላቀሉ 8 ተቋማት ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩና የገጠሟቸውን ችግሮች በቅንጅት መፍታት የሚያስችል እድል ለመፍጠር ያለመ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል።
በራሔል ፍሬው